የንፋስ ኃይል፤ የኢትዮጵያ የብርሃን አድማስ የአረንጓዴ ልማት ሌላኛው ብስራት!! - ኢዜአ አማርኛ
የንፋስ ኃይል፤ የኢትዮጵያ የብርሃን አድማስ የአረንጓዴ ልማት ሌላኛው ብስራት!!
በቁምልኝ አያሌው
የሰው ልጅ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን መጠቀም የጀመረው በጥንታዊ ሥልጣኔዎች ዘመን እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ለአብነትም፤ ግብፃውያን ከአምስት ሺህ ዓመታት በፊት ጀልባዎችን በባሕር ላይ ለመንዳት የንፋስ ኃይልን ይጠቀሙ ነበር። በሰባተኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ደግሞ ፋርስ (የአሁኗ ኢራን) የመጀመሪያውን በንፋስ ኃይል የሚሠራ የጥራጥሬ መፍጫ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ማዋል ጀመረች።
ግሪኮችና ሮማውያን የውሃ መንኮራኩሮችን በመጠቀም እህል መፍጨት የሚያስችል ፈጠራን እንዳስጀመሩ የታዳሽ ኃይል የታሪክ ማኅደሮች ይጠቁማሉ። ጥንታዊያን ሕዝቦች የፀሐይ ኃይልን ለብርሃንና ለሙቀት ምንጭነት ከመጠቀም ባለፈ፣ የፀሐይ ጨረርን በማሰባሰብ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚጠቀሙባቸውን ጥበቦች ነበሯቸው።
ምንም እንኳን የ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት በድንጋይ ከሰልና በተፈጥሮ ዘይት የበላይነት ቢያዝም፤ በዚሁ ወቅት ለታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ልማት መሠረት መጣሉን ታሪክ ያስትውሰናል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው እ.አ.አ በ1839 ፈረንሳዊ የፊዚክስ ሊቅ ኤድመንድ ቤኩረል፤ የፀሐይ ብርሃንን ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር የሚቻልበትን የ'ፎቶቮልታይክ' (Photovoltaic effect) ክስተት ማገኘቱ ነው። በተጨማሪም እ.አ.አ በ1882 የመጀመሪያው በውሃ ኃይል የሚሰራ የኤሌክትሪክ ማመንጫ በአሜሪካ ሥራ ጀመረ። እ.አ.አ በ1883 ደግሞ በኦስትሪያ ቪየና በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኤሌክትሪክ ኤግዚቢሽን፣ የንፋስ ኃይልን ወደ ኤሌክትሪክ የሚቀይሩ ተርባይኖችን ለመትከል የሚያስችሉ ወሳኝ የቴክኖሎጂ ዕድሎች ታይተዋል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ለታዳሽ ኃይል የሚሰጠው ትኩረት መቀዛቀዝ ቢያሳይም፣ በ1970ዎቹ የተከሰተው ዓለም አቀፍ የነዳጅ እጥረት ዓለም አማራጮችን እንድታማትር አስገድዷታል። በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መናር ሀገራት ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት ወደ ውሃ፣ ፀሐይና ንፋስ ኃይል ፊታቸውን እንዲያዞሩና በዘርፉ ለሚካሄድ ጥናትና ምርምር ከፍተኛ መነሳሳት እንዲፈጠር አድርጓል።
የንፋስ ኃይል ታሪካዊ ዳራና የቴክኖሎጂ እድገት
የንፋስ ኃይልን ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር ታሪክ እ.አ.አ በ1883 በኦስትሪያ ቪየና በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኤሌክትሪክ ኤግዚቢሽን ላይ ፍሬድላንድ በተሰኙ ሳይንቲስት አማካኝነት የመጀመሪያው የንፋስ ኤሌክትሪክ ተርባይን ለእይታ መቅረቡ ይነገራል። ይህ የፈጠራ ሥራ በየጊዜው እየተሻሻለ መጥቷል። በ1887 ስኮትላንዳዊው የኮሌጅ ፕሮፌሰር ጄምስ ብሊዝ የቤታቸውን መብራት ለማብራት የተጠቀሙበት የንፋስ ተርባይን በዘርፉ ትልቅ እመርታ ተደርጎ ይወሰዳል። ፕሮፌሰሩ ቀስ በቀስ የፈጠራ ውጤታቸውን አሳድገዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብም የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆን ያቸሉትን አድርገዋል።
የንፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታ በበርካታ ሀገራት የተለያዩ ሙከራዎች መደረጉን ድርሳናት ሲፈተሹ የሚያሳዩት እውነት ነው። ሆኖም ዘርፉ ትኩረት አግኝቶ እንዲያድግ ያደረገው በ1973 በዓለም ላይ የተከሰተው የነዳጅ ቀውስ ነው። ይህ ክስተት ሀገራት ወደ አማራጭ ኃይል ምንጮች እንዲያተኩሩ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ይህን ተከትሎም አሜሪካ መጠነ ሰፊ የንፋስ ኃይል እርሻዎችን (Wind Farms) በመገንባት ግንባር ቀደም መሆን ችላለች። እ.አ.አ እስከ 2008 ድረስ ከዘርፉ የምታመነጨውን የኃይል መጠን ወደ 24.4 ጊጋ ዋት አሳድጋለች።
የንፋስ ኃይል የማመንጨት ሂደት የንፋስን የተፈጥሮ እንቅስቃሴ በተርባይኖች አማካኝነት ወደ ሜካኒካዊ ኃይል፣ በመቀጠልም ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀይር ዘመናዊ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ነው። ሂደቱም የተርባይን ክንፎች በንፋስ ግፊት አማካኝነት በሚፈጥሩት ሽክርክሪት ጀኔሬተሩን በማንቀሳቀስ ኤሌክትሪክ እንዲመነጭ ያደርጋል።
የዓለማችን ግዙፍ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች የት ይገኛሉ?
በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ከ350 ሺህ በላይ የንፋስ ተርባይኖች ተተክለው ኃይል እየሰጡ ይገኛል። ቻይና በንፋስ ኃይል ማመንጨት የዓለማችን ቀዳሚ ሀገር ስትሆን፤ አሜሪካ እና ጀርመን በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። የቻይናው ጂኳን (Gansu) የንፋስ ኃይል ማመንጫም ከ20,000 ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም እንዲኖረው ታቅዶ እየተገነባ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
የንፋስ ኃይል በኢትዮጵያ
ዓለም ለታዳሽ ኃይል ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። ኢትዮጵያም በአፍሪካ የንፋስ ኃይል ልማት ቀዳሚ ተዋናይ የሚያደርጋትን ስራዎች እያከናወነች ነው። ሀገሪቷ በምስራቅ አፍሪካ ያላት ስትራቴጂካዊ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ የታደለችውን የተፈጥሮ ፀጋ ወደ አማራጭ ኃይል ለመቀየር ሰፊ ዕድል ፈጥሮላታል። በንፋስ ኃይል ልማት የመጣው ከፍተኛ ለውጥም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎትን በመሙላት የብዝኅ ታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማት እንዲጎለብት እያደረገ ይገኛል።
የተፈጥሮ ስጦታና ያልተነካው የኢትዮጵያ እምቅ የንፋስ ኃይል ፀጋ
ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አኳያ በንፋስ ኃይል አማራጭ እምቅ የመልማት ፀጋን ተችሯታል። በተለይም የታላቁ ስምጥ ሸለቆ፣ ሰሜናዊ ተራራማ ስፍራዎችና ምስራቃዊ ቆላማ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የንፋስ ፍጥነት ኃይልን ለማመንጨት ተስማሚ መልክዓ ምድሮች ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያ እስከ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሜጋ ዋት የንፋስ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህ አሃዛዊ መረጃም ከአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ኃይል የማመንጨት አቅም ጋር ሲነፃጸር ሰፊ የልማት ዕድል መኖሩን ያረጋግጣል።
ከጅምር እስከ ዛሬ የስኬት ጉዞ ምዕራፍ
የኢትዮጵያ የንፋስ ኃይል ልማት በ2001 ዓ.ም አሸጎዳ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀምሯል። በአዳማ 1 እና 2 ስራውን በማስፋት አሁን ላይ እስከ አይሻ 1 እና አሰላ ፕሮጀክቶች ደርሷል። እነዚህ የአዳማ፣ የአሸጎዳ፣ የአይሻ እና የአሰላ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አድማስ መስፋፋትን የሚያረጋግጡ ናቸው። ለሀገሪቷ አረንጓዴ ልማት ብስራት የሆኑ ታላላቅ ስራዎች ናቸው።
አዳማ-1 እና ሁለት፡- በአጠቃላይ 204 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው የአዳማ የኤሌከትሪክ ማመንጫዎች የኢትዮጵያን የንፋስ ኃይል የማመንጨት አቅም በተግባር ያረጋገጡ ፋና ወጊዎች ናቸው።
አሸጎዳ፡- በፈረንሳይ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የተገነባ ሁለተኛው የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው። 120 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ይህ ጣቢያ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሚገኙ ዜጎች ከሚሰጠው ብርሃን በተጨማሪ የኢንዱስትሪ አቅም ሆኗል።
አይሻ-2፡- በቅርቡ ተመርቆ ወደ ስራ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ 80 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። በኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር አቅራቢያ መገናባቱም ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው።
አሰላ፡- በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የምትገኝ የኢትዮጵያ ብርቅየ አትሌቶች መፍለቂያ ስፍራ ናት። በስንዴና ገብስ የግብርና ምርታማነትም በተምሳሌትነት ትጠቀሳለች። ነፋሻማ የአየር ሁኔታዋም ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅም የሚሆን ፀጋን ተችሯታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚያዚያ 08 ቀን 2018 ዓ.ም 100 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚያስችለውን የአሰላ ንፋስ ኃይል መርቀዋል። በዚሁ ወቅትም አርሲ በስንዴና ገብስ ብቻ ሳይሆን በንፋስ ኃይልም የኢትዮጵያ ብልፅግና ማዕከል መሆኗን የአካባቢውን የብዝኅ ፀጋ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የአሰላ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም ኢትዮጵያ ከዕዳና ኪሳራ ወጥታ ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜ ማጠናቀቅና ማትረፍ መጀመሯን በተግባር ያሳየ ነው። ከዚህም በላይ በንፋስ እና በጂኦተርማል ኃይል ማመንጫዎች የኢነርጂ ማዕከል እየሆነ መምጣቷን ያረጋግጣል።
"አርሲ በኃይል ዘርፍ ልክ እንደ ስንዴ እና ገብስ ተጨማሪ አቅም ያለው አካባቢ መሆኑን ማየት ችለናል" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በንግግራቸው። የአሰላ ንፋስ ኃይል ማመንጫ በ145 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የተገነባ መሆኑን በመጥቀስ፤ ፕሮጀክቱ በአዋጭነት ደረጃ ሲታይ እጅግ ስኬታማ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የሚወሰዱ ብድሮች ለትውልድ ዕዳ ትተው የሚያልፉ እንደነበሩ በማስታወስ፣ የአሁኑን ፕሮጀክት የተለየ የሚያደርገውን ነጥብ ሲያነሱ ይህ ፕሮጀክት ቢበዛ በሁለት ዓመት ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ ትርፋማ ስለሚሆን ልጆቻችን ትርፍ ሀብት የሚያገኙ እንጂ ዕዳ የሚረከቡ አይሆኑም በማለት ነው የገለጹት። ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ግማሹን በእርዳታ እንዲሁም ቀሪውን ከወለድ ነጻ በሆነ ብድር ላቀረበችው የዴንማርክ መንግሥት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል። የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱም ቢበዛ በሁለት ዓመት ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ ትርፋማ ስለሚሆን ልጆቻችን ምንዳ እንጂ ዕዳ የሚረከቡ እንደማይሆን አስገንዝበዋል።
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ኢተያ ላይ በደማቅ ሁኔታ የተመረቀው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት የጀመረችውን ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ሌላኛው ታሪካዊ አሻራ ነው። በመደመር መንግስት መፅሐፍ ገፅ 206 ላይ እንደተጠቀሰው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት ባለፉት ዓመታት ሰፊ ኢንቨስትመንት ተካሂዷል። ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትም ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል። የታላቁ ሕዳሴ የኃይል ማመንጫን ጨምሮ ሌሎች በጅምር ያሉና በሚገባ አገልግሎት እየሰጡ ያልነበሩ ማመንጫዎችን ወደ መስመር ለማስገባት ተችሏል። በዚህም ሀገራችን ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚያስፈልጋትን የኃይል አቅርቦት በሚገባ መሸፈን ችለናል በማለት ተከትቧል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች 504 ሜጋ ዋት ኃይል ብሔራዊ የኃይል ቋትን በመመገብ የኃይል አቅርቦት የጀርባ አጥንት ሆነዋል።
በኢትዮጵያ የንፋስ ኃይል ልማት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ
ቀደም ሲል የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በመንግስት ብቸኛ ይዞታነት ብቻ ሲካናወኑ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ግን ይህን አሰራር የሚቀይር የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጓል። ባለሃብቶች በመንግስትና የግል አጋርነት (PPP) ማዕቀፍ የሚሳተፉበት ሰፊ ዕድል ለመፍጠር ተችሏል። ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ከማበረታታቱም በላይ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የግሉን ዘርፍ በኃይል ልማት ላይ ለማሳተፍ የተወሰዱት የፖሊሲ እርምጃዎች አሁን ላይ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ጀምረዋል። ለአብነትም፤ በሶማሌ ክልል በመንግስትና በግል አጋርነት የሚገነባው የአይሻ-1 እና 3 የንፋስ ኃይል ፕሮጀክት ከ300 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።
የኢትዮጵያ የንፋስ ኃይል ልማት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የኃይል ትስስር በማጠናከር ለጋራ ዕድገት መፋጠን ጉልህ ፋይዳ አለው። ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባትና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቀነስ ረገድ የምትከተለው የልማት መንገድ ለሌሎች ሀገራትም ተምሳሌት የሚሆን ነው።
የኢትዮጵያ የንፋስ ኃይል ከብርሃን ባሻገር
የንፋስ ኃይል የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት በማሟላት ለሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ስትራቴጂክ መሰረት እየጣለ ይገኛል። ለአብነትም በኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ እያበረከተ ያለውን ፋይዳ መጥቀስ ይቻላል።
የኢነርጂ ዋስትና እና የኃይል ምንጭ ስብጥር፡- በኢትዮጵያ ከውሃ ኃይል የማመንጨት ተግባር ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል። ይህም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚከሰት የድርቅ አደጋ የኃይል አቅርቦት ተጋላጭነት በማስፋት ተፅዕኖ ያሳድራል። የንፋስ ኃይልም የአቅርቦት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጉልህ ስትራቴጂክ ፋይዳ አለው። በበጋ ወራት የውሃ መጠን ሲቀንስ የንፋስ ኃይልን በመጠቀም ደግሞ የተፈጥሮ ሚዛንን የጠበቀ አስተማማኝ የኃይል ስብጥር ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ ያበረክታል።
የኢንዱስትሪ መፋጠንና የሥራ ዕድል፡- የኃይል አቅርቦት ለአስተማማኝ የኢንዱስትሪ ምርታማነት የጀርባ አጥንት ነው። የኢንዱስትሪው ዘርፍ ደግሞ ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው። በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገነቡ የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች የዕውቀትና የምርታማነት ሽግግርን በማፋጠን ረገድ ፋይዳቸው የጎላ ነው።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በንፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ተከላና ጥገና ወቅት የዜጎችን የምህንድስና ክህሎት በማጎልበት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በተጨባጭ ያጠናክራሉ። ፋብሪካዎች አስተማማኝ ኃይል እንዲያገኙ በማድረግ የገቢ ምርቶችን የመተካትና የወጪ ንግድ አቅማቸውን በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
ቀጣናዊ ትስስርና የውጭ ምንዛሬ ግኝት፡- የኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከልነት አቅም የሚያጎለብቱ ከአነስተኛ እስከ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፤ በመገንባታ ሂደትም ናቸው። የንፋስ ኃይል ልማትም ቀጣናው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን እየደገፈ ይገኛል። ይህም የዕድገት ትስስርን በማፋጠን በየዓመቱ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያበረክታል።
የአረንጓዴ አሻራና የአካባቢ ጥበቃ፡- የንፋስ ኃይል ከብክለት የፀዳ ንፁህ የኃይል ምንጭ ነው። ይህም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት የተቸራትን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማፅናት በቀላሉ አይታይም። የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ የፋይናንስ ገቢን በማሳደግም ተጨማሪ የታዳሽ ኃይል ልማትን ለማጠናከር ያስቻላል። የገጠሩን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት በማስፋትም የአካባቢና የደን መራቆትን ለመቀነስ ያስቻል።
የንፋስ ኃይል ልማት ለኢትዮጵያ ቅንጦት አይደለም፤ ይልቁንስ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዕድገትን የማፋጠን የህልውና ጉዳይ ነው። ለዚህም የንፋስ ኃይል ፀጋዎችን በማልማት ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የንፁህ ኢኮኖሚ ግንባታ ፋና ወጊነት የሚያረጋግጥ የልማት አቅጣጫ ተተልሞ እየተሰራበት ነው። የኢትዮጵያ የንፋስ ኃይል ልማትም አዲስ ተስፋን የፈነጠቀ የብርሃን አድማስና የአረንጓዴ ልማት ሌላኛው ብስራት እየሆነ ይገኛል።