በድሬደዋ የሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሕበረሰቡ ዘንድ ባህል እየሆነ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ የሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሕበረሰቡ ዘንድ ባህል እየሆነ መጥቷል
ድሬደዋ ፣ ሚያዚያ 9/2018(ኢዜአ)፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሕብረተሰቡን የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶች ይበልጥ እያጠናከረ መምጣቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ገለፀ፡፡
የኮሚሽኑ የወጣቶችና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ በሐር አብደላ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ ባለፈው የክረምት ወራት በተካሔደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 320 አዳዲስ ቤቶች ተገንብተው አረጋውያንና አቅመደ ካሞች እንዲረከቡ ተደርጓል።
በተጨማሪም 159 የአረጋውያን ቤቶችን በማደስም የተሻለ ኑሮ እንዲመሩ ለማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በክረምቱ ወቅት የተገኙ ውጤቶችን በበጋው ወራትም አጠናክሮ በማስቀጠል 85 ሺ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ 11 አይነት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያላቸው ልማቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም በተጠናቀቁት የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዩች የአፅዋማት ወቅት ማዕድ የማጋራት እና ችግረኞችን የመደገፍ ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ከ23ሺ በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውንም ነው ያመለከቱት።
በዋናነትም በደም ልገሳ፣ በማዕድ ማጋራት ፣ ህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከልና ሰላምን በመጠበቅ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከልና የጎርፍ መከላከያ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን ወሳኝ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል ።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የችግረኞችን መሠረታዊ ማህበራዊ ችግሮችን ከመፍታት በዘለለ መንፈሳዊና አካላዊ እርካታና ደስታ የሚሰጥ መሆኑን የገለፀው ደግሞ በድሬድዋ አስተዳደር የወረዳ 2 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤል ምስራቅ ነው።
ይሄንን መሠረት በማድረግ ባለፈው ክረምትና በተያዘው የበጋ ወራት 39 የአረጋውያንን ቤቶችን በተቀናጀ መንገድ መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል ።
ከቤቶቹ በተጨማሪ ወጣቶች ማዕድ በማጋራት፣ በፅዳትና ውበት ጥበቃ፣ የአካባቢን ሰላምና ፀጥታ ተደራጅተው በመጠበቅ የላቀ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሺ የሚቆጠሩ ችግረኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት ደስተኛ ቤተሰብ ለመፍጠር እያገዘ መሆኑንም አንስተዋል።