በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሰብአዊ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሰብአዊ ድጋፍ ተደረገ
አርባ ምንጭ፤ ሚያዚያ 10/2018(ኢዜአ)፦ በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሰብአዊ ድጋፍ ተደረገ።
ዛሬ የሰብአዊ ድጋፉን ያደረጉት የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እንዲሁም የጋሞ አብያተ ክርስቲያናት የጋራ ልማት እና የጋሞኛ ቋንቋ ስብከተ ወንጌል ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ናቸው።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያዊያን በመረዳዳትና በመደጋገፍ የዳበረ ባህል አላቸው።
በዚህም ተቋሙ 24 ቅርንጫፎችን በማስተባበር በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው የምግብና የቁሳቁስ ድጋፎችን ለጋሞ ዞን አስተዳደር ማስረከባቸውን ተናግረዋል
በአደጋው ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ በመሆኑ ዛሬ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እንዲሁም የጋሞ አብያተ ክርስቲያናት የጋራ ልማት እና የጋሞኛ ቋንቋ ስብከተ ወንጌል ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በጋራ 1 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሰብአዊ ድጋፍ አድርገዋል።
በድጋፉ ብርድ ልብስ፣ የአዋቂና የህፃናት አልባሳት፣ ጫማዎችና ሌሎች ቁሶችም መካተታቸውተመላክቷል።
የድጋፉ አስተባባሪ ተወካይ አቶ ጡጋሞ ያልሶ ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመታደግ ድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።