በዞኑ ሞዴል አርሶ አደሮችን ወደ ኢንቨስትመንት የማሻገር ስራ እየተሰራ ነዉ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ሞዴል አርሶ አደሮችን ወደ ኢንቨስትመንት የማሻገር ስራ እየተሰራ ነዉ
ጅማ፤ ሚያዚያ 10/2018(ኢዜአ)፡- በጅማ ዞን ሞዴል አርሶ አደሮችን እና በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተዉ ስኬታማ የሆኑ ማህበራትን ወደ ኢንቨስትመንት የማሸጋገር ስራ እየተካሔደ ነዉ።
በጅማ ዞን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሰፋፋ የመጣዉን የመሠረተ ልማት ግንባታ ተከትሎ በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑም ተገልጿል።
በተያዘው ዓመትም 1 ሺህ 680 ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ማስገባቱን የዞኑ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ፅህፈት ቤት አመልክቷል።
የፅህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዘሊካ ቡላ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤በተያዘው ዓመት በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ 20 ማህበራት፣ 39 የህብረት ስራ ማህበራትን ጨምሮ በድምሩ 1 ሺህ 680 ፕሮጀክቶች ወደ ኢንቨስትመንት ገብተዋል።
ወደ ኢንቨስትመንት ከገቡት 1 ሺህ 680 ፕሮጀክቶች ውስጥ ደግሞ 1 ሺህ 621 የሚሆኑት ሞዴል አርሶ አደሮች መሆናቸውን ነው የገለጹት፤
ወደ ኢንቨስትመንት የገቡት ባለሃብቶችም 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸዉንም ነው ያመለከቱት።
ለኢንቨስትመንት ስራዉ 7 ሺህ 578 ሄክታር መሬት መሰጠቱን የገለፁት ስራ አስኪያጇ ለፕሮጀክቶቹ ተግባራዊነት ጠንካራ የሆነ ክትትልና ደጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዞኑ ለኢንቨስትመንት መሬት ተረክበዉ ወደ ስራ መግባት ያልቻሉትን በመለየትም የፋይናንስ እና የሊዝ ማሽን አቅርቦት ችግር ያለባቸውን በመለየት ከባንክ ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተው አስፈላጊዉ ድጋፍ ተደርጎላቸዉ ወደ ስራ መግባት ያልቻሉ ባለሀብቶች ፍቃዳቸዉ የሚሰረዝበት አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የጠቀሱት።
በሌላ በኩል በተቋም ደረጃ አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን እና የማቀላጠፍ ስራ ትኩረት የተሰጠዉ ሲሆን ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ የተንዛዙ አሰራሮችን በማስቀረት የተሻለ አገልግሎት እየተሰጠ ነዉ ብለዋል።