ቀጥታ፡

በዞኑ የበጋ ወራት የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራዎች ምርታማነት እንዲጨምር አድርገዋል

አዳማ፤ ሚያዚያ 10/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጋቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዞኑ በየዓመቱ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የአካባቢ መራቆትን ከማሻሻል ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።


 

ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎቹ የውሃ ምንጮች እንዲጎለብቱ በማድረግ ለመስኖ ልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራው የአፈር ለምነት እንዲጨምር እና በጎርፍ ይጠረግ የነበረን ለም አፈር በማስቀረት   የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን አስረድተዋል።

የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎች በተከናወነባቸው ተፋሰሶች ላይ በክረምቱ ወራት ችግኞችን በመትከልና በመንከባበከብ ህብረተሰቡ በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን በቅንጅት መሰራቱንም አውስተዋል።

በስራውም አርሶ አደሮች፣ ወጣቶችንና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።

የልማቱን ውጤታማነት ለማስቀጠልም በዘንድሮው የበጋ ወራት በ270 ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ ማከናወን ተችሏል ብለዋል

ከተከናወኑ ተግባራት በዋናነት 54 ሺህ 693 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የተለያዩ የእርከን ሥራዎች መሰራታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሰፋፊ የእርጥበት ማቆያ መዋቅሮችን ጨምሮ የተለያዩ ስነ-አካላዊ እና ስነ-ሕይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በስፋት መከናወናቸውን አቶ አብነት ጠቅሰዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች የተፋሰስ ልማት ስራ ጠቀሜታውን በመረዳታችን በየዓመቱ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሳተፋቸውንም  አንስተዋል።

በአካባቢያቸው በተሠራው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ጎርፍን በመከላከልና የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ለሰብል ምርታማነት ጉልህ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም