በክልሉ ከ919 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል አገኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ919 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል አገኝተዋል
ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ919 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል መፈጠሩን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተር ፕራይዞች ልማት ዳይሬክተር አቶ ስላባት ሰውአገኝ ለኢዜአ እንደገለፁት ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።
በዚህም በበጀት ዓመቱ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተይዞ በተደረገ ሁሉን አቀፍ ጥረት በዘጠኝ ወሩ ለ919 ሺህ 475 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል።
የስራ ዕድሉ ከተፈጠረባቸው መስኮች መካከልም ከ125 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑት በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መሆኑን ገልጸዋል።
የስራ ዕድሉ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች መሆኑን ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በድምሩ ለ919 ሺህ 475 ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት 1 ሺህ 347 የመስሪያ ሼዶች እንዲሁም ለከተማ ግብርና፣ ለማዕድን ማውጫና ለሌሎች የግብርና ልማት ተግባራት 11 ሺህ 444 ሄክታር መሬት ለኢንተርፕራይዞች መተላለፉንም ተናግረዋል።
የመስሪያ ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ኢንተርፕራይዞች ከ5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አቅርቦት የተመቻቸ ስለመሆኑም አንስተዋል።