በአማራ ክልል የበልግ ወቅት እስካሁን ከ241 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብሎች እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የበልግ ወቅት እስካሁን ከ241 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብሎች እየለማ ነው
ደሴ ፤ሚያዚያ 10/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የበልግ ወቅት እስካሁን ከ241 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብሎች መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትንና የዘንድሮውን የበልግ ወቅት ልማት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም የክልሉን የግብርና ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በያዘነው የበልግ ወቅት ከ245 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱን አስታውሰው እስካሁን ከ241 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብሎች መሸፈን ተችሏል ብለዋል።
አሁን እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ ለሰብል ልማት ተስማሚ በመሆኑ በተለይም የስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ቦለቄ፣ ማሾ፣ አተር፣ ምስርና ሌሎችንም ሰብሎች መዝራት ስለመቻሉ ተናግረዋል።
የልማት ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ዶ/ር ማንደፍሮ በበልጉ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰሜን ሽዋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ችሮታው አስፋው፤ በዞኑ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአካባቢውን ምቹነት መሰረት ያደረጉ የግብርና ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የበልጉን ዝናብ በመጠቀም በዞኑ እስካሁን ከ86 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው ከዚህም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የሚገኝ ይሆናል ብለዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን የተሁለደሬ ወረዳ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋጨፋ ወረዳ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች በዘንድሮው የበልግ ውቅት የእስካሁኑ እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑን አንስተው ከፍተኛ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።