ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10 /2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከመቀሌ 70 እንደርታ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ፋሲል ከነማ በ42 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። መቀሌ 70 እንደርታ በ26 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያሸነፈው ፋሲል ከነማ በድል ጉዞው ለመቀጠል ይጫወታል። ካሸነፈ የሁለተኝነት ደረጃን ከመቻል የመረከብ እድል ያገኛል።

በ27ኛ ሳምንት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 ያሸነፈው መቀሌ 70 እንደርታ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል። ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ለሚያደርገው ትግል ወሳኝ ነው። 

በሌላኛው መርሐ ግብር ምሽት 12 ሰዓት ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ29 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ34 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። 

ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ወልዋሎ ማሸነፍ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ወሳኝ የሚባል ነው።

በ27ኛ ሳምንት በሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና 1 ለ 0 የተሸነፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት  እስከ ሚያዚያ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ሲዳማ ቡና በ51 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

አቤል ያለው ከሲዳማ ቡና በ12 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በ10 ጎሎች ይከተላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም