የኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ለሰላምና አብሮነት በኃላፊነት ስሜት መስራት ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ለሰላምና አብሮነት በኃላፊነት ስሜት መስራት ይገባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ለተከታዮቻቸው ኃይማኖታዊ አስተምህሮን ከማስረጽ ባሻገር ለሀገር ሰላምና አብሮነት በኃላፊነት ስሜት መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኃይማኖት ዘለቀ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ባለፉት ሶስት ወራት በኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ላይ ያደረገውን የይዘት ስርጭት ክትትልና ግምገማ ውጤት ይፋ ማድረጊያ መርሀ ግብር አዘጋጅቷል።
"የኃይማኖት ተቋማት የመገናኛ ብዙኃን ለሰላምና አብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው መርሐ ግብር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ ኢድሪስ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እና የኃይማኖት ተቋማት የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኃይማኖት ዘለቀ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙሃን ለህብረተሰቡና ለተከታዮቻቸው ኃይማኖታዊ አስተምህሯቸውን ከማድረስ ባሻገር አብሮነትን፣ መረዳዳትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ልማትን እና የጋራ ዕሴቶችን በማስረፅ አዎንታዊ አበርክቶ አላቸው።
ከለውጡ በፊት በነበሩት የመገናኛ ብዙኃን ሕጎች የኃይማኖት ተቋማት የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን እንዳያቋቁሙ፣ ሕጋዊ ዕውቅና እና ፈቃድ እንዳያገኙ ተከልክለው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ሀገራዊ የሚዲያ ሪፎርም ሲደረግ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ እና አዋጅ እንዲሻሻል በማድረግ የኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃንም በሕግ ዕውቅና እና የብሮድካስት ፈቃድ በማግኘት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ከሁሉም የኃይማኖት ተቋማት ጋር በመቀናጀት፤ የተቋማቱ መገናኛ ብዙሃን በሕግ በተሰጣቸው ዕውቅና መሰረት ፈቃድ አውጥተው እንዲንቀሳቀሱ አስፈላጊውን የክትትልና ድጋፍ ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት በኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ላይ ላለፉት ሶስት ወራት ያካሄደውን የክትትልና የግምገማ ውጤት ሪፖርት በማቅረብ የጋራ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል ብለዋል።
ከ51 በላይ የሚሆኑ የኃይማኖት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ በማግኘት በሥርጭት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በዲጂታልና በማህበራዊ ሚዲያዎች በኩል ኃይማኖታዊ መልዕክት ለተከታዮቻቸው እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ጥቂት የማይባሉት ሕግን የሚተላለፉ፣ ኃይማኖታዊ ዕሴቶችን የሚሸረሽሩ፣ የማህበረሰቡን ባህል እና እሴት የማይወክሉና ሃላፊነት የጎደላቸውን ይዘቶች የሚያሰራጩ እንዳሉም አመልክተዋል።
የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን የሀገሪቱን ሕጎች እና የሃይማኖታዊ ዕሴቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ አቅርበዋል።
በኃይማኖት ሚዲያዎች የሚሰራጩ ይዘቶች ለሁሉም ሀይማኖቶች እና እምነቶች ተገቢ ክብር የሚሰጡ፣ የኃይማኖትና የእምነት ነጻነትን፣ መሰረታዊ ሰብዓዊ መብትን የሚያከብሩ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሀፊና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ አባል ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ የኃይማኖት ተቋማት ለሀገር ሰላምና አብሮነት የጎላ አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ኃይማኖት፣ የጥንታዊ ስልጣኔና የብዝሃ ማንነት ባለቤት መሆኗን ገልጸው፤ የኃይማኖት ተቋማት የዘመናት የሰላም ምንጭ ሆነው መቆየታቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም መንፈሳዊ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ብዝሃነትን እንደ ጌጥ በመቁጠር የዜጎችን ትስስርና አንድነት ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ ከፈጣሪ የተሰጣቸውን የርህራሄና የፍቅር ትምህርት ወደ ጎን በመተው የጥላቻ ንግግር የሚያራምዱ፣ በኃይማኖት ስም የሚነግዱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ በመግለጽ፤ የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።