ቀጥታ፡

የመዲናዋ የልማት እመርታ የኢትዮጵያን ገፅታ በማጉላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ የልማት እመርታ የኢትዮጵያን ስምና ገፅታ በማጉላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አርባ ስድስት ሜዳ ተብሎ የሚጠራውን የስፖርት ማዘውተሪያ መርቀው ለህዝብ አገልግሎት ክፍት አድርገዋል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ወጣቶች ስፖርት ወዳድ መሆናቸውን አስተዳደሩ በፅኑ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

በዚህም ወጣቶች ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ እንዲያገኙ ለማስቻል በየሰፈሩ የስፖርት መሠረተ ልማት በስፋት እየተገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በመዲናዋ የሚገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወጣቶችን በአካልና በአዕምሮ እንዲጎለብቱ ለማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ የስብዕና መገንቢያ ማዕከላትም የኢትዮጵያን ርዕይ የሚያሳካ ብቁና ጤናማ ትውልድ ለመቅረፅ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

መዲናዋም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ እየተሰራች መሆኑን አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ግዞ የሚያቆም አንዳች ኃይል የለም፤ ልማታችንም በታላቅ ቁጭትና ወኔ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በአዲስ አበባ መጪውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ የሚገነቡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችም የኢትዮጵያን ስምና ገፅታ በማጉላት ወሳኝ ሚና እያበረከቱ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የልማት እመርታዎች ዕዳን ወደ ምንዳ በመቀየር ለሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና መሠረት እየጣሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ምቹ፣ ጽዱና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያጎናፅፉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም