ቀጥታ፡

የቼልሲ እና ማንችስተር ዩናይትድ የሊጉ ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 33ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል።

በዕለቱ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ምሽት አራት ሰአት ላይ ቼልሲ ከማንችስተር ዩናይትድ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ቼልሲ በ48 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።  ማንችስተር ዩናይትድ በ55 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።  

ቡድኑ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመግባት ያለውን ተስፋ ለማለምለም ጨዋታውን ማሸነፍ ግድ ይለዋል። 

በ32ኛ ሳምንት በሊድስ ዩናይትድ 2 ለ 1 የተሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።


 

ማንችስተር ዩናይትድ ማሸነፍ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን ለማረጋገጥ የበለጠ ይቃረባል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከብራይተን ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ይጫወታሉ።

የሰሜን ለንደኑ ቶተንሃም በ30 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ብራይተን በ46 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ባለፉት 14 የሊግ ጨዋታዎች ድል የናፈቀው ቶተንሃም ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። 

ብራይተን ካሸነፈ በሊጉ አራተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል። 

ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ላይ ብሬንትፎርድ ከፉልሃም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ሊድስ ዩናይትድ ከዎልቭስ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከቦርንማውዝ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም