ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን በመጪው ክረምት ሚተከሉ ከ916 ሺህ በላይ የቡና ችግኞች ተዘጋጅተዋል

ደብረ ማርቆስ ሚያዚያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን በመጪው ክረምት ሚተከሉ 916 ሺህ በላይ የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸው ተገለፀ።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ተሾመ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት ፤ በመጪው የክረም ወር ከ320 ሄክታ በላይ በሆነ መሬት ላይ የሚተከሉ 916 ሺህ የቡና ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

 በዋናነትም የአካባቢውን ስነ ምህዳርና የአየር ንብረት ተስማሚነት በማረጋገጥ ለቡና ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በቡና ልማቱም 25 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 320 ሄክታር በላይ መሬትን ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ችግኞቹ በመንግስት፣ በማህበራትና በግለሰቦች ችግኝ ጣቢያዎች ፈልተው የተዘጋጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩን በተለያዩ የግብርና አማራጮች በማሳተፍ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ እንዲችል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

በዞኑ በደብረ ኤሊያስ፣ በማቻከልና በጎዛምን ወረዳዎች በኩታ-ገጠም እየተካሄደ ያለውን የቡና ልማት በማጠናከር በቀጣይ በሁሉም ወረዳዎች ተደራሽ የማድረግ ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በማቻከል ወረዳ የውላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብነት ይርዳው፤ ቡናን በኩታ ገጠም ለማልማት ከግማሽ ሄክታር በላይ መሬት እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገነት አያሌው በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ካለሙት ቡና እያገኙ ያለውን ጥቅም ለማስፋት በክረምቱ የሚተከል ከሩብ ሄክታር በላይ ማሳቸውን እያዘጋጁ  መሆናቸን ገልጸዋል።

 ለዚህም  6 ሺህ በላይ የቡና ችግኞችን ማፍላታቸውን ጠቁመው ከራሳቸው የሚተርፈውን በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

 በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተደረገ ጥረት 5 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በቡና መልማቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም