ቀጥታ፡

ሕይወትን መለወጥ እንደሚቻል በተግባር እያረጋገጠ ያለው የከተማ ግብርና

የሌማት ትሩፋት አካል በሆነው የከተማ ግብርና በመሰማራት ሕይወትን መለወጥ እንደሚቻል በተግባር እያሳየን ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በዘርፉ የተሰማሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለፁ።

የከተማ ግብርና በከተማ ውስጥ በሚገኙ አነስተኛ ቦታዎች፣ መኖሪያ ግቢዎች፣ ጣራዎች ወይም አጥሮች ላይ ቀላል ቁሳቁሶችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ እንስሳትና ዓሳ በማምረት ህይወታቸውን የሚቀይሩበት የምርት ስርዓት ነው።

ይህ ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ ባለፈ ለሴቶችና ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድልን በሰፊው የሚፈጥር ነው፤ በመፍጠር ላይም ይገኛል።

መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወደ ተግባር የገባው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም በገጠርም ሆነ በከተማ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ነው።

በአዲስ አበባ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ተጠቃሚዎችም በዘርፉ መሰማራታቸው የዕለት ተዕለት የቤት ፍጆታቸውን ከመሸፈን አልፎ አዋጭ የገቢ ምንጭ በመሆን ሕይወታቸውን በተጨባጭ እየቀየረላቸው እንደሚገኝ ነው ለኢዜአ የሚገልጹት።


 

በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ የተሰማራው የወልዳ ወሊኒ ማህበር ሰብሳቢ ተካልኝ ደበሌ በ2014 ዓ.ም መንግሥት ለከተማ ግብርና ስራ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ ማህበራቸው ወደ ከተማ ግብርና ስራ መግባቱን ይገልጻሉ።

ማህበሩ በአሁኑ ሰዓት ሰባት አባላት ያሉት መሆኑን በመጠቆም የተለያዩ የአትክልት ምርቶችን በማምረት ለራስ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የከተማ ግብርና ስራ በስፋት ያላተለመደ ተግባር እንደነበረ አንስተው፤ አሁን ላይ በግብርና ስራ ላይ የሚሰማሩ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ያነሳሉ።


 

ሌላኛው በእንስሳት እርባታ ላይ የተሰማራው ወጣት አወቀ አበባው እንደሚለው ዶሮዎችንና የወተት ላሞችን  በማርባት ተጠቃሚ በመሆን ላይ ነው።

እንቁላል እና የተለያዩ ወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ በማቅረብ ገበያ የማረጋጋት ስራ እየሰሩ መሆኑን ይናገራል።

በዘርፉ የተሰማሩት እነዚህ ተጠቃሚዎች፣ በከተማ ግብርና ተሰማርቶ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በተጨባጭ እያረጋገጡ መሆኑን ያስረዳሉ።

ሌሎች ዜጎችም መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመርና በአካባቢያቸው ያለውን ሀብት በመጠቀም፣ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የእንስሳትና ሀብትና መኖ ልማት ባለሙያ አሰፉ ሙላቱ እና የሆርቲካልቸር ባለሙያው ማሙሽ አሳምነው እንደሚሉት በመዲናዋ የከተማ ግብርና ስራ ባህል እየሆነ መምጣቱን ይገልጻሉ።


 

በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የተሻሻሉ ምርት ዝርያዎችን መጠቀም እንዲችሉ፣ምርትን ሲያመርቱ ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ሙያዊ እገዛዎችን እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም