ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ዓለም አቀፍ ቅቡልነት የሚያረጋግጥ አቅም እየተፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የሚሰጡ የፍተሻ፣ የኢንስፔክሽንና የሰርተፊኬሽን አገልግሎቶችን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሚያረጋግጥ አቅም እየተገነባ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መዓዛ አበራ ገለጹ።

ኢንጂነር መዓዛ አበራ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የሀገሪቱን ምርቶችና አገልግሎቶች የጥራት ደረጃ በማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅትም 124 የላብራቶሪ ፍተሻ ወሰኖች በዕውቅና ሰጭ አካል ኦዲት ተደርጎ ውጤቱ እየተጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢንፔክሽን ዘርፍ በተሰራ ስራም በግብርና ምርት፣ በታሸጉ ምግቦች፣ በኬሚካል፣ በዌር ሀውስና በሊፍት ኢንስፔክሽን 16 ወሰኖችን ማስጠበቅ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመትም በታወር ክሬን፣ በቧንቧ ውሃ ናሙና እንዲሁም በዘይትና በዱቄት ቫይታሚን ማበልጸግ ዘርፎች ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘት ማመልከቻ መቅረቡን ጠቁመዋል።

በሰርተፊኬሽን ዘርፍም 47 ነባር የዓለም አቀፍ ዕውቅናዎችን በማስጠበቅ በዘንድሮው ዓመት ብቻ በ16 አዳዲስ ወሰኖች ላይ ዕውቅና ማግኘት መቻሉን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም 23 ወሰኖችን በመለየት ለዓለም አቀፍ ዕውቅና የሚረዳ የሰነድ ዝግጅትና የአቅም ግንባታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በዘንድሮ ዓመትም በአሉሚኒየም፣ በቆርቆሮ፣ በሚስማርና በሴራሚክ ምርቶች ላይ አዲስ ዕውቅና መገኘቱን ተናግረዋል።

በአካባቢ ጥበቃና በትምህርት አስተዳደር ሥርዓት የተገኘው ዓለም አቀፍ ዕውቅናም ድርጅቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎት በማንኛውም ዓለም ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመጨረሻም ድርጅቱ ግቦችን ለማሳካት ከብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም