ፓራጓይ የአውሮፓ ወዳጅነት ዋንጫን አነሳች - ኢዜአ አማርኛ
ፓራጓይ የአውሮፓ ወዳጅነት ዋንጫን አነሳች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ):- የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ያዘጋጀው እና በቱርኪዬ ሲካሄድ የቆየው የ"UEFA Frendship Cup" ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።
በፍጻሜው ጨዋታ ፓራጓይ ኖርዌይን 1 ለ 0 በመርታት የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።
በውድድሩ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ባደረገው ጨዋታ በቱርኪዬ ተሸንፎ አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ቱርኪዬ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ኮስታሪካ ሞሮኮን በመለያ ምት 5 ለ 4 በመርታት አምስተኛ ሆና ስትጨርስ ሞሮኮ ስድስተኛ ደረጃን ይዛለች።
ዩራጓይ ኡዝቤኪስታንን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ሰባተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በውድድሩ በሁሉም ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደችው ኡዝቤኪስታን የመጨረሻውን ስምንተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ከመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ሲያካሂድ የቆየው የወዳጅነት ዋንጫ ከውድድር ባለፈ የክፍለ አህጉራዊ እግር ኳስ ልማት ትብብርን ማጠናከርን ያለመ ነው።
በተጨማሪም የእርስ በእርስ የልምምድ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን የተለያዩ ስልጠናዎች እና ጉብኝቶችም የውድድሩ አካል ነበሩ።