ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ልማቱን ለማጠናከር የተጀመረው ጥረት ይጠናከራል

ድሬዳዋ፣ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በመሰብሰብ፣ የሕዝብን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የመፍታት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ገለጹ።

የድሬዳዋ አስተዳደር የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የመጪው በጀት ዓመት የትኩረት መስኮች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄዷል።


 

አቶ ሀርቢ ቡህ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የገጠርና የከተማውን ነዋሪ መሠረታዊ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ልማቶች አበረታች ናቸው።

በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራትም የተቀመጡ የልማት ውጥኖችን በላቀ ደረጃ ዳር ለማድረስ የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ስኬታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህን አበረታች ውጤቶች ይበልጥ ለማሳደግ፣ የገጠሩን አርሶ እና አርብቶ አደር የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ድሬዳዋን የኢንዱስትሪ፣ የኢንቨስትመንት እና የሎጀስቲክስ ማዕከል የማድረግ ጉዞን በውጤት ለመደምደም የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሚፈለገውን ለውጥና ውጤት ለማስመዝገብም የአስተዳደሩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚያመነጩትን ገቢ አሟጦ የመሰብሰብ ሥራ በቅንጅት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሥራ አፈጻጸም ግምገማው ላይ እንደተመለከተው፤ በዘንድሮው ዘጠኝ ወራት 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ የተሰበሰበው 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 80 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ፤ የተሰበሰበው ገቢ ከታቀደው ዕቅድና ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት አንጻር አነስተኛ መሆኑን አንስተዋል።


 

የአስተዳደሩን ነዋሪዎች የልማት ጥያቄዎች በተሻለ ደረጃ ለመፍታትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቀሪዎቹ ሦስት ወራት ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ ጉዳይ በትኩረት መሠራት ይኖርበታል ብለዋል።

ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዘጠኝ ወራቱ በገጠርና በከተማ የተሠሩ ሰው ተኮር ልማቶች የሕዝብን አንገብጋቢ ጥያቄዎች በመፍታት ነዋሪው በልማቱ ላይ የባለቤትነት ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በቀሪ የበጀት ወራት የተሻለ ሥራ በመሥራት የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት እንደሚተጉም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም