ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከመኸር እርሻ ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ለማግኘት ወደ ስራ ተገብቷል

ኮምቦልቻ፤ ሚያዚያ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል  ከመኸር እርሻ ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ለማግኘት  ወደ ስራ መገባቱን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለፁ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ የ2018/19 መኸር ምርት ዘመን የሰብል ልማትና ጥበቃ ንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሄዷል።


 

በመድረኩ ላይ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ በተሻሻሉ አሰራሮች የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ተግባሩን በማስቀጠልም በ2018/19 የመኸር ሰብል ልማት 5 ነጥብ 58 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በማልማት ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የመኸር ሰብሉን ውጤታማ ለማድረግም ለግብዓትና ለቴክኖሎጂ አቅርቦት ትኩረት በመስጠት ለምግብ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎች በስፋት እንደሚመረቱ ተናግረዋል።

ለዚህም የአደረጃጀት፣ የኩታ-ገጠም ልማት፣ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች ዘመናዊ አሰራሮችን መተግበር እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ በበኩላቸው፣ በቴክኖሎጂና በተሻሻለ አሰራር ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክልሉ በሰብል ልማት  እየተመዘገበ የመጣውን ምርታማነት  በማጠናክር በሄክታር 36 ነጥብ 3 ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ  እየተሰራ  መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም የግብዓት አቅርቦት፣ የእርሻ ማሳ ዝግጅት፣ የባለሙያ ስልጠናና ሌሎችም ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው ለዘንድሮው የመኸር ሰብል ልማት እየተደረገ ካለው የእርሻ ዝግጅት በተጨማሪ ግብዓት በስፋት እየተሰራጨ ነው ብለዋል።

በተሻሻለ አሰራር ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት ለኢንዱስትሪዎችና ለገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

በዞኑ በ2018/19 የምርት ዘመን ከ561 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በማልማት ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት ደግሞ የሰሜን ሽዋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ችሮታው አስፋው ናቸው።

አሲዳማ መሬትን በማከም፣ በኩታ-ገጠም በማልማት፣ በመስመር በመዝራትና ሌሎችንም የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም