ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና በምርምር ሥራዎች ሚናቸውን እያጠናከሩ ነው

አርባ ምንጭ፤ ሚያዚያ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና በምርምር ሥራዎች ያላቸውን ሚና እያጠናከሩ መምጣታቸው ተገለጸ።

"ሳይንስ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ 12ኛው ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ቦጋለ ገብረማሪያም (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለፖሊሲና ስትራተጂ ግብአት የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችና የሰለጠነ የሰው ሀይል ማፍራት ላይ አተኩረው እየሰሩ ነው።


 

በእስካሁኑ ሂደትም ተቋማቱ የሚያቀርቧቸው የጥናትና ምርምር ሥራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው ዕድገት ለማምጣት እያገዙ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ዛሬ የተጀመረው አውደጥናትም የዚሁ አካል እንደሆነ ጠቁመው፣ በአውደጥናቱ በሕክምናና ጤና ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ እና በግብርና ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ ብለዋል።

ጥናታዊ ጽሁፎቹ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑበትን  ሂደት ለማቀላጠፍ አውደጥናቱ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

በመድረኩ የጥናት ጽሁፍ ካቀረቡት መካከል አበበ መንክር (ዶ/ር) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ሥራዎች  ሀገሪቱን  ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ለሚደረገው ጥረት የራሳቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ተቋማት የሰው ሀይል ከማፍራት ጎን ለጎን ምርምሮችን በማድረግ ለሀገር ልማት አበርክቷቸውን እያጠናከሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።


 

ዛሬ በተጀመረው አውደ ጥናትም በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ የጥናት ውጤቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ብለዋል።

ጥናትና ምርምሮቹ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግና በአጭር ግዜ ውስጥ ከተረጂነት ለመውጣት የሚያስችሉ መሆናቸውንም ነው አበበ (ዶ/ር) ያነሱት።

ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በመንግስት ለቴክኖሎጂ ሽግግር የተሰጠውን ትኩረት ማሳደግና የአልሚ ባለሀብቶች እና አርሶ አደሮችን ቅንጅት ማሳደግ ላይ ተጨማሪ ሥራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል። 

ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር የመቀየሩ ሥራ ይበልጥ ሊሰራበት እንደሚገባ ያነሱት ደግሞ ሌላው በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉት ተመራማሪ  የማነህ ተክላይ (ዶ/ር) ናቸው።

እንደእሳቸው ገለጻ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዲፈቱ  ወደ ተግባር ሊለወጡ ይገባል።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተመራማሪዎች፣ የምርምር ተቋማት እና የመንግስት አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም