ቀጥታ፡

መሠረተ ልማት የኢኮኖሚው የደም ሥር እና የብልጽግና መሠረት ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ መሠረተ ልማት የኢኮኖሚው የደም ሥር፣ የብልጽግናም መሰረት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ እየተገነባች ነው በሚል መሪ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንት ዛሬ ከፍተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው መሠረተ ልማት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ግብአቶችን በማመላለስ የኢኮኖሚው የደም ሥር እና የብልጽግና መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዐውደ ርዕዩ የተመለከቱትም ወሳኝ የልማት ተቋማት መሠረተ ልማትን እንደ ሀገር በቅንጅትና በትብብር የመምራት አዲስ የሥራ ባህል እየገነቡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታት ፈጠራን፣ ፍጥነትን እና ጥራትን የጉዞ መርሕ በማድረግ ተጨባጭ ስኬቶች መመዝገባቸውን ነው የገለጹት።

የመንገድ ርዝመት በብዙ ኪሎ ሜትሮች ማደጉን፣ የታዳሽ ኃይል የማመንጨት ዐቅም ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት አካባቢ መድረሱን፣ እንዲሁም በዲጂታል ዘርፍ የሞባይል ተጠቃሚዎች 97 ሚልዮን፣ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ደግሞ 57 ሚልዮን መድረሳቸውን በዝርዝር አቅርበዋል።

በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተባበርን የማይቻል የለም የሚለውን መርሕ በተግባር ያሳዩ፣ ፍጥነትና ጥራትን ያስተሣሠሩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውንም አክለዋል።

የመንግሥትን የልማት ጉዞ ለማጣጣል ለሚሞክሩ አካላት እውነታውንና ፍርዱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትተን ሥራችንን እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ለማበልጸግና ለመገንባት በየበረሃውና በየተራራው እየፈሰሰ ላለው ላብና ደም ተገቢውን ክብር እንሰጣለን ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

መንግሥት በመንገድ፣ በኃይል፣ በመስኖ፣ በባቡርና በዲጂታል መሠረተ ልማት ዘርፍ ፈጣንና ፍትሐዊ ልማት ለማረጋገጥ የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት የሥራ፣ የውጤት እና የተስፋ ዘመን መሆኑን በመጥቀስ፤ ትናንት የተገነባው ለዛሬ፣ ዛሬ የሚገነባው ደግሞ ለነገው ትውልድ ኩራት እና የብልጽግና ዋስትና መሆኑን አስገንዝበዋል።

 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም