የጤና ነገር … - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ነገር …
በዮሐንስ ደርበው
ማዲያት ታክሞ ይድናል? እነማንንስ ያጠቃል?
የሥነ-ውበት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሱመያ ኑርሁሴን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ስለማዲያት መንስዔ፣ ምልክቶች እና ሕክምና ሙያዊ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። እንደ ባለሙያ ቢደረግ ያሉትንም መክረዋል።
• ማዲያት እነማንን ያጠቃል?
ማዲያት ማንኛውንም ሰው እንደሚያጠቃ ያነሱት ዶ/ር ሱመያ፤ በብዛት ግን በሴቶች ላይ እንደሚከሰት ያስረዳሉ።
በዚህም መሠረት ይላሉ፤ እርግዝና ላይ ያሉ እንዲሁም የወሊድ መከላከያ የሚወስዱ ሴቶች እና ሆርሞናል ቴራፒ ላይ ያሉ ሰዎች በስፋት ለማዲያት ተጋላጭ ናቸው።
በተጨማሪም በብዛት ምግብ ማብሰል (ኪችን) ላይ የሚሠሩ ሰዎች ለማዲያት እንደሚጋለጡ ጠቁመዋል።
ባብዛኛው ማዲያት የሚያጠቃው በዕድሜ ከ25 ወይም ከ30ዎቹ በላይ የሆኑትን መሆኑንም አንስተዋል።
• መንስዔ
እንደ ዶክተር ሱመያ ገለጻ፤ ለማዲያት ከሚያጋልጡ መንስዔዎች መካከል ዋነኛው የፀሐይ ጨረር ነው።
በተጨማሪም ሆርሞናል ፋክተር (የወሊድ መከላከያ መጠቀም፣ እርግዝና ላይ መሆን፣ ሆርሞናል ቴራፒ መውሰድ) ለማዲያት አጋላጭ መንስዔ ሆነው ይጠቀሳሉ ይላሉ።
ጭንቀት እንዲሁም ቆዳን የሚያስቆጡ ነገሮች ለማዲያት አጋላጭ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።
• ምልክቶች
ማዲያት ቀላ፣ ጠቆር ወይም ደብዘዝ ያለ ቀለም (መልክ) ይዞ ከትንሽ ጀምሮ የሚሰፋ መሆኑን ዶክተር ሱመያ አስገንዝበዋል። ለምሳሌ ይላሉ፤ ጉንጭ ላይ መውጣት ቢጀምር ወደ ሁለቱም ጉንጮች ከዚያም ወደ ግንባር እንዲሁም አገጭ እና አፍንጫ ሊደርስ እንደሚችል ገልጸዋል።
በሂደትም የማቃጠል፣ የመቆጥቆጥ እና ማሳከክ ሁኔታ ሊኖረው እንደሚችል ነው ያነሱት።
• ሕክምና
መንስዔዎቹን ዐውቆ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ የሕክምናው አካል መሆኑን ያስገነዘቡት ዶክተር ሱመያ፤ የፀሐይ ጨረር መከላከያዎችን መጠቀም፣ በሕክምና የሚሰጡ መድኃኒቶችን ሳያቋርጡ በትዕግስት መጨረስ (ቶሎ ለውጥ አላየሁበትም ብሎ አለማቋረጥ) እንደሚገባም መክረዋል።
የማዲያት ሕክምና ስኬታማነቱ ለሁሉም ሰው በዕኩል ጊዜ እንደማይታይ በመግለጽ፤ እንደተከሰተበት ጊዜ ከሰው ሰው እንደሚለያይ በአጽኦት ተናግረዋል። ለምሳሌ አሉ፤ ዓመታት ያለፉት ማዲያት እና 2 ወራት የሆኑት ሕክምና እኩል ቢጀመርም በተመሳሳይ ጊዜ ላይድኑ እንደሚችሉ አመላክተዋል። ስለዚህ የሌላኛው ድኖ የኔ አልዳነም በሚል ሕክምናን ማቋረጥ ስህተት መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በሌላ በኩል ማዲያትን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል አረጋግጠው፤ ይህም የሚሆነው መንስዔዎቹን በማወቅ የማዲያት ተጋላጭ ባለመሆን ነው ብለዋል።
ከተቻለ በየሥድስት ወሩ ወይም በየዓመቱ የቆዳ ጤና ምርመራ ማድረግ እና ያለበትን ደረጃ ማወቅም የሚከሰት ችግር ቢኖር እንኳ ሥር ሳይሰድድ በማከም ቶሎ እንዲድን ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።