የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያሳልጡ መሠረተ ልማቶች በልዩ ትኩረት እየተገነቡ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያሳልጡ መሠረተ ልማቶች በልዩ ትኩረት እየተገነቡ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያሳልጡ መሠረተ ልማቶች በልዩ ትኩረት እየተገነቡ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
''ኢትዮጵያ ትገነባለች፤ ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ጥራት ለመሰረተ ልማት እመርታ'' በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ሳምንት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዛሬ ተከፍቷል።
መድረኩን በይፋ የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሥራ፣ የውጤት እና የተስፋ ዘመን ላይ ትገኛለች ብለዋል።
የለውጡ መንግሥት የሚከተለው የመደመር ዕሳቤም ካለፈው መልካሙን በማስቀጠል፣ ዛሬን ተግቶ በመስራት ለነገ የሚተርፍ አሻራ ማሳረፍ መሆኑን ገልጸዋል።
መሠረተ ልማትን በተቀናጀ መንገድ የመምራት አዲስ ባህል እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ በከተማና ገጠሩ ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ዋጋ ለሚከፍሉ ወገኖች ክብር መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
መንግሥት የኢትዮጵያን ብልፅግና በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆም እና ለማሳለጥ መሰረተ ልማትን በልዩ ትኩረት እያጠናከረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከልማትና ብልፅግና ጉዟችን ለአፍታም አንዘናጋም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአንጻሩ ለውጡን የሚያጣጥሉ ወገኖች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ለእነዚህ ወገኖችም እኛ እነሱን ለማስረዳት የምናጠፋው ጊዜ የለም፤ ስራችንን እንቀጥላለን፤ እውነታውንና ፍርዱን ለኢትዮጵያ ህዝብና ለእውነተኛ ፈራጆች እንተዋለን ሲሉ ገልጸዋል።
መሠረተ ልማት የኢኮኖሚ ዕድገት የደም ሥር መሆኑን በመግለጽ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት አስደማሚ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በመንገድ ሽፋኑም ከ126 ሺህ ኪሎ ሜትር ወደ 182 ሺህ ኪሎ ሜትር ማደጉን፣ በአቪዬሽን ዘርፍም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብቱ የላቁ ስኬቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በዲጂታል ተደራሽነትና በኮሪደር ልማት ዘርፎችም የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ የሚያፋጥኑ እመርታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታዩ የጊዜ፣ የጥራትና የወጪ ውስንነቶችን ለመቅረፍ የተወሰዱ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችም የዘርፉን ውጤታማነት በማስጠበቅ ስኬት መገኙቱን አብራርተዋል።
የመንግሥት ከፕሮጀክት ግንባታ ወደ ሥርዓት ግንባታ የተሸጋገረበት ስልታዊ አቅጣጫም ለሀገራዊ ብልፅግና ጉዞ ስኬት መሠረት መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የኮንስትራክሽን ሳምንትም የመደመር መንግሥትን የልማት እይታና ሀገራዊ ራዕይ ያስተሳሰረ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።