ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራ አቁመው የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል

ጎንደር፤ ሚያዚያ 9/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራ አቁመው የነበሩ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

 ''እኛም እንሸምት'' በሚል መሪ ሃሳብ በጎንደር ከተማ ሲካሔድ የቆየው ኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈራ ታረቀኝ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ አምራች ኢንዱስሪዎች የሚያነሷቸውን ችግሮች በመፍታት ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

በዚህም ባለፉት 9 ወራት ውስጥ ማምረት ያቆሙና ወደ ማምረት ያልገቡ 137 ከፍተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል።

በዚሁ ወቅትም  ሶስት ሺህ ለሚጠጉ ባለሀብቶችም የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።


 

ኢንዲስትሪዎቹ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉላቸው በማድረግ ፣የግንባታ ቦታዎችን በፍጥነት በማቅረብና  የፋይናንስ ችግሮቻቸውን  በመፍታትም ነው ስራ እንዲጀምሩ የተደረገው ብለዋል፡፡ 

በዚህም ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል በመፍጠር ፣ ተኪና ለወጭ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን በማቅረብ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ነው የገለጹት።

በክልሉ ከ17ሺ በላይ ባለሀብቶችና ባለ ድርሻ አካላት የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረኮች መካሄዳቸውን ጠቁመው መድረኮቹም ችግሮችን ተቀራርቦ ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ጠቅሰዋል።

በጎንደር ከተማ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ 5 የኢንዱስትሪ መንደሮች ተቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡


 

ጎንደር ከተማ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ለሚሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምቹና ተመራጭ መሆኑዋን ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ግርማይ ልጃለም በበኩላቸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 10 መካከለኛና አንድ ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ገብተዋል ነው ያሉት።

በከተማው በኤክስፖርት ምርት የተሰማሩ 7 አምራች ኢንዱስትሪዎች 17ሺ ቶን ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ  143 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማስገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡


 

በተኪ ምርት የተሰማሩ 99 አምራች ኢንዱስትሪዎች 38 ሺህ ቶን የሚጠጋ ምርት በማምረት ከ149 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንዳስቻሉም አመልክተዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ ባለሀብቶች በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ በግንባታና በመሰረተ ልማት አቅርቦት ረገድ  ያደረገላቸው ድጋፍ ፈጥነው ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ እንዳገዛቸው አስረድተዋል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ ባለሀብቶች ተሳታፊ ሲሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ያቀረቡበት ኤግዚቢሽንም ተመርቆ ተከፍቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም