ቀጥታ፡

ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ላላቸው ቀጣናዊ ኮሪደሮች የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል- የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ላላቸው ቀጣናዊ ኮሪደሮች ፈጣን የፋይናንስ አቅርቦት እንዲመቻች አሳሰቡ።

የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው።

28ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባም ጎን ለጎን ተካሂዷል።


 

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በሚኒስትሮች ስብሰባው ላይ ተሳትፈዋል።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላትና የንግድ እንቅስቃሴዋ ሙሉ በሙሉ በቀጣናዊ ትስስር ላይ ለተመሰረተ አገር፣ ቀልጣፋ የትራንስፖርት ኮሪደሮች አማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በኢኮኖሚ ኮሪደሮች ላይ የሚደረግ ፈጣን የኢንቨስትመንት ንግድን ለማቀላጠፍ፣ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት እና በቀጣናው የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

እነዚህን ኮሪደሮች ቀጣናዊ ዕድገት፣ ትስስርና ዕድል የሚፈጠርባቸው ዋነኛ ሞተሮች ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለቀጣናዊ ኮሪደሮች የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ እንዲጠናከርም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ስብሰባው ከ9 ሺህ 100 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ እና 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የተመደበላቸውን አራት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ኮሪደሮች አፈጻጸም ገምግሟል።

የልማት አጋሮች ከእ.አ.አ 2019 ጀምሮ ለኮሪደሮቹ ግንባታ የሚውል 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አሰባስበዋል።

ምንም እንኳን መሻሻሎች ቢታዩም፣ ቀጣናውን ሙሉ በሙሉ ለማስተሳሰር ወሳኝ በሆኑ የመንገድ ክፍሎች ላይ አሁንም የፋይናንስ ክፍተት መኖሩን ሚኒስትሮቹ አመልክተዋል።

ውይይቱ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ እና አፈጻጸምን ለማፋጠን በሚያስችሉ አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮች ላይ ትኩረት አድርጓል።

በስብሰባው ላይ የፋይናንስ ክፍተቶችን በመሙላትና ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን የኮሪደር ፕሮጀክቶች በማፋጠን የቀጣናውን የኢኮኖሚ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ የጋራ አቋም መያዙን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም