የኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻነት የሚያጎለብት ምቹ ምኅዳር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻነት የሚያጎለብት ምቹ ምኅዳር ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻነት የሚያጎለብት ምቹ የአሰራር ምኅዳር መፈጠሩን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጤና ሥርዓቱን በማዘመን ብቃት ያለው የቴክኖሎጂ፣ የሰው ሃብትና የግብዓት አቅም እየተፈጠረ ነው።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ኢትዮጵያን ሕክምና ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርግ ግብ በማስቀመጥ ምቹ አሰራር ምኅዳር ተፈጥሮ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
የሕክምና ቱሪዝም ተወዳዳሪነትን ለማጎልበትም የጤና ሙያተኞች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የአቅም ግንባታ ስልጠና የሚወስድ ሙያተኞችም ዓለም አቀፍ የሙያ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የሕክምና ተቋማት የቴክኖሎጂና ግብዓት የማሟላት ውጤታማ ተግባራትም ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ብቻ ይሰጡ የነበሩ የካንሰርና ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችን በክልሎች በማስፋት ዜጎች በአቅራቢያቸው አገልግሎት የሚያገኙበት ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
የጤና ተቋማትን የማዘመን ሥራም ለሕክምና ወደ ውጭ የሚጓዙ ዜጎችን እንግልት በመቀነስ ዓለም አቀፍ የጤና ቱሪዝም ተወዳዳሪነት እያጎለበተ መሆኑን አንስተዋል።
የዓለም አቀፍ የሙያ ማረጋገጫ ስታንዳርድ ጸድቆ ወደሥራ መግባቱም የግልና የመንግስት ጤና ተቋማትን አገልግሎት የበለጠ ለማዘመን ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት የሙያ ማረጋገጫ ስታንዳርድም ሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ዜጎችን የሕክምና አገልግሎት እምነት የሚያጎለብት መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም በኢትዮጵያ የሚኖሩና ከውጭ የሚመጡ ዜጎችን የጤና አገልግሎት ፍላጎት በማሟላት የሕክምና ቱሪዝም ለማስፋት ገንቢ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ለኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የሰጠው ዕውቅናም የጤና ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ወሳኝ አቅም እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
በቅርቡ ወደሥራ የሚገባው የኢትዮጵያ የመድኃኒትና የምግብ የምርምር ልህቀት ማዕከላት ለጤናው ዘርፍ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አስታውቀዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት የማዘመን ሥራ በማጠናከር የሕክምና ቱሪዝም ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።