የዘላቂ የዕዳ አስተዳደር የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ስትራቴጂካዊ ትኩረት ነው -የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የዘላቂ የዕዳ አስተዳደር የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ስትራቴጂካዊ ትኩረት ነው -የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዘላቂ የዕዳ አስተዳደርን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አካል አድርጋ እየሰራች እንደምትገኝ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።
የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ መካሄዱን ቀጥሏል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ ከስብሰባው ጎን ለጎን ዓለም አቀፍ የመንግስታት ዕዳ (Global Sovereign Debt) የተመለከተ ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ በውይይቱ ወቅት፤ በዕዳ ውስጥ ባሉ አገራት፣ በሁለትዮሽ የመንግሥታት አበዳሪዎች፣ በግል አበዳሪዎች እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መካከል ገንቢና ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲኖር መድረኩ ለሚጫወተው ሚና ያላትን አድናቆት ገልጻለች።
ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያ በቡድን 20 (G20) የጋራ ማዕቀፍ አማካኝነት እያከናወነችው የሚገኘውን የዕዳ ሽግሽግ (debt restructuring) ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
የድርድር ሂደቱ ከአጋሮች ጋር ያለውን ጠንካራ ትብብር የሚያንፀባርቅ ከመሆኑም በላይ፣ መንግሥት የዕዳ ዘላቂነትን ለማረጋገጥና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በገለጻቸው፤ የዕዳ ሽግሽግ ስምምነቱ ግቡን እንዲመታ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀና ፈጣን ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
የሪፎርም ስራዎቿን ለማስቀጠልና ምጣኔ ሀብታዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ፤ ከአበዳሪዎችና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሚጠበቀው ገንቢ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጥሪዋን አስተላልፋለች።
ኢትዮጵያ የዘላቂ የዕዳ አስተዳደርን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አካል አድርጋ እየሰራች መሆኑንና ይህም የፊስካል ዲሲፕሊን፣ የሀገር ውስጥ ሀብት አሰባሰብ እና አካታች ዕድገት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጻለች።
መንግሥት ስልታዊ የሆነ የዕዳ አስተዳደርን በመከተል፣ ከዕዳ ሽግሽግ የሚገኙ ዕድሎችን ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለልማት ግቦች ለማዋል ያለውን ጽኑ አቋም በድጋሚ ገልጿል።
ኢትዮጵያ በውይይቱ ላይ መሳተፏ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ግንኙነቶች ያላትን ንቁ ተሳትፎና የዕዳ ተጋላጭነትን በጋራ ለመፍታት ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል።