ቀጥታ፡

በግብርናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ደዋጨፋ፤ሚያዚያ 9/2018(ኢዜአ)፡-የክልሉን ሰላም በማጽናት በግብርናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለፁ።

የፌዴራል፣ የአማራና የአፋር ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዳዋጨፋ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ  የፍራፍሬ ችግኝ ተከላን ዛሬ አስጀምረዋል።


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ የክልሉን ሰላም በማጽናት የህብረተሰቡን ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በተለይም በግብርውና ዘርፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና የተሻሻለ አሰራርን በመተግበር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በክልሉ አካበቢን መሰረት ያደረገ የልማት አቅጣጫ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመው ዛሬ የተጀመረው  ኩታገጠም የፍራፍሬ ልማትም ይህንኑ ከግምት  ያስገባ ነው ብለዋል።

የተጀመረውን የፍራፍሬ ልማት ወደ አፋር ክልል አጎራባች ወረዳዎች በማስፋት ጥራት ያለው የፍራፍሬ ምርትን ከአገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ  ለማቅረብ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሀጅ አወል አርባ በበኩላቸው የሁለቱን ክልል የህዝብ ለህዝብ ትስስር በልማትም አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ አቋም ተወስዷል ብለዋል።

በዚህም ዛሬ የተጀመረው የፍራፍሬ ልማት የሁለቱን ክልሎች አዋሳኝ ወረዳዎችን አካቶ በመተግበር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነም ገልፀዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)፣ በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች ያለውን ፀጋና ሀብት በጥናት ለይቶ በማልማት ለሀገር ብልፅግና ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ  በጥራት፣ በአይነትና በብዛት በማምረት ከፍጆታ አልፎ ለወጭ ንግድ የሚተርፍ አመራረት ላይ በማተኮር ውጤት እየተገኘ መሆኑንም  ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለው ኩታ ገጠም የፍራፍሬ ልማት ለአገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ድርሻው የጎላ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም