ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማጎልበት ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤን ብላክ ጋር የከፍተኛ ደረጃ ምክክር አደረጉ።


 

ውይይቱ በኢትዮጵያ እና በፋይናንስ ኮርፖሬሽኑ (DFC) መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በተለይም እንደ ትራንስፖርት እና ማዕድን ባሉ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች ትብብርን ማስፋት ላይ የሀሳብ ልውውጥ አድርገዋል።

ሁለቱ ወገኖች ዘላቂ እና አካታች እድገትን ለማፋጠን የልማት ፋይናንስ ያለውን ወሳኝ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይም መክረዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶችን አብራርተዋል።

መንግስት ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተለይም በመሠረተ ልማት እና በሌሎች ስትራቴጂካዊ ዘርፎች በኢትዮጵያ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለውን ፍላጎት በድጋሚ ገልጿል።

ሁለቱም ወገኖች የፋይናንስ ዕድሎችን ለመጠቀም እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ውጤቶችን ለማምጣት የቀጣይ ትብብር አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ሁለቱ ወገኖች ትብብራቸውን ለማጠናከር እና በኢትዮጵያ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የኢንቨስትመንት ኢኒሼቲቮች ለማሳለጥ የጋራ ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም