ቀጥታ፡

በደቡብ ኦሞ ዞን የበልግ ወቅት የችግኝ ተከላ ሥራ ተጀመረ

ዲመካ፣ ሚያዚያ 9/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኦሞ ዞን በተያዘው የበልግ ወቅት ከ4 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞች ተከላ ሥራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ የ2018 ዓ.ም የበልግ ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላ ዛሬ በዲመካ ከተማ ተጀምሯል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንላርገው አዲሱ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በዞኑ በዘንድሮ የበልግ ወቅት ከ4 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞች ይተከላሉ። 


 

ህዝቡን በማሳተፍ ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሀግብር  ከ2 ሚሊዮን በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ተዘጋጅተው ዛሬ የመትከል ሥራው በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል።

የችግኝ ተከላ ሥራው ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ጎን ለጎን እንደሚካሄድ ገልጸው፣ ለግጦሽ ሣር የሚሆን ሥፍራን የመከለል ሥራም አብሮ ይከናወናል ብለዋል።

እንደኃላፊው ገለጻ ዘንድሮ የሚተከሉት ችግኞች የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የሚያግዙ፣ ለምግብነት እና ለገቢ ምንጭነት የሚውሉ ፍራፍሬዎች እንዲሁም ለጥላነት የሚያገለግሉ ናቸው። 

በደቡብ ኦሞ ዞን ዲመካ ከተማ ዛሬ በተጀመረው የበልግ ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሀሃ ግብር ችግኝ ተከላ ላይ የተሳተፉት አቶ ናደው ኤካደ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ቀደም ሲል የተተከሉ ችግኞች ለተፈጥሮ አደጋ የነበራቸውን ተጋላጭነት እንደቀነሱላቸው ተናግረዋል።

ልማቱ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በአግባቡ በመረዳታቸው በተያዘው የበልግ ወቅትም ሆነ በመጪው የክረምት ወቅት በሚካሄድ የተከላ መርሀግብር የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እና የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄዎች ተጨባጭ ውጤት እንዳመጡ የጠቀሱት ደግሞ አቶ ስጦታው አመዴ ናቸው።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች በተሰሩባቸው አካባቢዎች ተጨባጭ ለውጦች እንደመጡ ገልጸው፣ በተለይ ተራቁተው በነበሩ አካባቢዎች ችግኝ በመተከሉ እያገገሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም