ቀጥታ፡

ከዓለም አቀፍ የፍትሕ ተቋማት ጋር መሥራት የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፍ የለውጥ ሥራዎችን ለማጠናከር ይረዳል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፡- ከዓለም አቀፍ የሕግና ፍትሕ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት በሀገራችን እየተተገበሩ ያሉ የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፍ የለውጥ ሥራዎችን በይበልጥ ለማጠናከር የጎላ ድርሻ አለው ሲሉ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ገለጹ።

በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው የተመራ ልዑክ በአውሮፓና የኤዥያ ሀገራት የዳኝነትና የፍትሕ ተቋማት የሥራ ጉብኝት አድርጓል።

በዚህም በሲንጋፖር፣ በሆንግ ኮንግ፣ በፈረንሳይ እና በኔዘርላንድ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን መጎብኘቱን እና ከተቋማት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉን አቶ ዓለምአንተ ለኢዜአ አስረድተዋል።

የጉብኝቱ ዓላማም፤ እንደ ሀገር እና በክልል ደረጃ የተጀመሩ የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ የለውጥ ሥራዎችን በይበልጥ እያጠናከሩ ለመሄድ የሚያስችል ልምድ መቅሰም መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተጨማሪም በቀጣይ በተመረጡ መስኮች ላይ ከተቋማቱ ጋር በትብብር መሥራት የሚቻልበትን ምቹ መደላድል መፍጠር መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከጉብኝቱ ጎን ለጎንም አቶ ዓለምአንተ ከሲንጋፖር ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ግሎሪያ ለም፣ ከዓለም አቀፍ የሽምግልና ማዕከል ሴክሬታሪ ጀነራል ተርሳ ቺንግ (ፕ/ር)፣ ከሆንግ ኮንግ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆዋኒ ላዑ እና ከሆንግ ኮንግ ዓለም አቀፍ የሕግ ማሰልጠኛ ተቋም የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ኃላፊ ጄምስ ዲንግ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገዋል።

እንዲሁም በፈረንሳይ ከዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል ፕሬዚዳንት ክላውዲያ ሰሎሞን፣ ከፓሪስ የግልግል ዳኝነት ማዕከል ፕሬዚዳንት ሃፌዝ ቨርጅ፣ ከዓለም አቀፍ ቋሚ የግልግል ፍርድ ቤት ምክትል ሴክሬታሪያት ጀነራል ጋርት ስኮፊልድ እና ከ ዘ ሄግ ዓለም አቀፍ የሕግ ትምህርት ተቋም ምክትል ሴክሬታሪያት ጄነራል እና ቫሲልቫ እና በግልግል ዳኝነት ላይ ከሚሠሩ የጥብቅና ማኅበራት ተወካዮች ጋር መክረዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም አቶ ዓለምአንተ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተጀመሩ እና የተሠሩ ሰፋፊ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እና ሁለንተናዊ የተቋም ግንባታ የለውጥ ሥራዎችን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ተደራሽ እና ውጤታማ የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት እና ፍርድ ቤቶችን ለማዘመን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አስረድተዋል።

በተለይም አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን ለማጠናከር እንደ ሀገር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ጨምሮ በፍርድ ቤቶች የተመዘገቡ የለውጥ ሥራ ውጤቶችን እና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎችን ብሎም የትብብር መስኮችን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ትስስር የፈጠረላት በመሆኑ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት እና በሰፋፊ የኢኮኖሚ፣ የሕግና የተቋም ግንባታ ማሻሻያ ውስጥ እያለፈች በዚህም ሀገሪቱን የግልግል ዳኝነት ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ሥራ አስቻይ ሁኔታዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን ለማጠናከር በተያዘው የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፍ ዕቅድ ላይ ዓለም አቀፍ የሕግና የፍትሕ ተቋማት እንዲሁም ሀገራቱ በትብብር መሥራታቸው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው በአጽንዖት ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ ተቋማቱ አመራሮች በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፍ እንዲሁም በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ውጤታማነት አድንቀዋል።

በቀጣይም በባለሙያ ዐቅም ግንባታ፣ በቴክኒክ ድጋፍ እና ልምዶችን በማጋራት ረገድ በትብብር ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት ለልዑኩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም