በክልሉ ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን በማስፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው- ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን በማስፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው- ቢሮው
ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 8/2018( ኢዜአ)፡-ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን ግንባታ በማስፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለፀ።
በክልሉ ባላፉት ዘጠኝ ወራት አንድ ሺህ 131 ሄክታር መሬት ማልማት ያስቻሉ ዘመናዊ የመስኖ ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገልጿል።
በክልሉ በመስኖ መልማት የሚችል ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ያለ ቢሆንም እስካሁን በዘመናዊ መንገድ ወደ ልማት የገባው ከ242 ሺህ ሄከታር የሚበልጥ አይደለም።
የቢሮው የመስኖ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አየልኝ መሳፍንት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዘመናዊ የመስኖ ተቋማት ግንባታ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም አርሶ አደሩን ከልማዳዊ አሰራር በማላቀቅ የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚ እንዲሆን የግንባታ ቦታዎችን በጥናት በመለየት ወደ ስራ ለማስገባት ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ነው የገለጹት።
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 23 መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ አንድ ሺህ 131 ሄክታር መሬት ማልማት እንደተቻለ ገልፀዋል።
በመስኖ ተቋማቱም ከ3 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም ከ100 ያላነሱ የመስኖ ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ለመስኖ ተቋማቱ ግንባታ ለተያዘው ዓመት ብቻ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተሰራ ሲሆን በቀሪ ወራትም ሌሎች በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘመናዊ መስኖ መስፋፋት እንደ ሃገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማሳካት ተይዞ እየተከናወነ ያለውን ግብ ውጤታማ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
የመስኖ ተቋማቱ ግንባታ ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል በመፍጠርም በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እያስቻሉ መሆኑንም አንስተዋል።
በክልሉ በወንዝ ጠለፋና መሰል ባህላዊ የመስኖ ልማት መንገድ 481 ሺህ ሄክታር መሬት እየለማ እንደሆነም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።