ኢትዮጵያ ለኮፕ 32 ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁማ የዝግጅት ስራዎችን እያከናወነች ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለኮፕ 32 ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁማ የዝግጅት ስራዎችን እያከናወነች ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለኮፕ 32 ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁማ የዝግጅት ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የኮፕ 32 አስተናጋጅ እንደሆነ ሀገር፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮሚቴ በይፋ በማቋቋም ዝግጅቷን ቀደም ብላ ጀምራለች ብለዋል።
ሂደቱን በግልጽ ግብ እና በላቀ ምልከታ ለመምራት ቁልፍ አመራር መመደቡና የኮፕ ፕሬዝደንት መዋቅርም የተቀናጀና የላቀ ውጤት የሚያስገኙ የቅድሚያ ተግባራቱን መጀመሩን ገልጸዋል።
ዛሬ ከብሔራዊ ኮሚቴው ጋር በነበራቸው ስብሰባ በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም ክፍተቶችን የመለየት እና ጥረቶች ከሀገራዊ ርዕይ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸው መዳሰሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በመድረኩ የጋራ ቀጣይ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመው፤ ትኩረቱም በጠንካራ ትብብር፣ በተዋሃደ ታላቅ ርዕይ እና በጋራ ጽኑ ትጋት ተናቦ ይህን ዓለም አቀፍ ሁነት በልህቀት በማስተናገድ የሀገርን ታላቅነት ዳግም ማሳየት መሆኑን አስታውቀዋል።