በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የክላስተር የፍራፍሬ ልማት ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የክላስተር የፍራፍሬ ልማት ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናወነ
ደዋጨፋ፤ሚያዝያ 9/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደና በአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የሚመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ በክላስተር የሚካሄድ የፍራፍሬ ልማት ችግኝ ተከላ አስጀምሯል።
ከርዕሳነ መስተዳድሮቹ በተጨማሪ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣እንዲሁም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር)ና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ተገኝተዋል።
በተጨማሪም ሌሎች የክልል፣የዞን አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመርሃ ግብሩ ታድመዋል።
በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፣የዞኑ ስነ-ምህዳርና የአየር ንብረት ለፍራፍሬ ልማት ምቹ ነው።
ዞኑ በገፅና በከርሰ ምድር ውሃ የታደለ በመሆኑ ያለውን ጸጋ በመጠቀም የኩታ-ገጠም የፍራፍሬ ልማት ስራን በዛሬው እለት በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።
ይህም እስካሁን በተበጣጠሰ መልኩ ሲካሔድ የነበረውን የፍራፍሬ ልማት ወደ ኩታ ገጠም በማስፋት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታልሞ እየተሰራ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም የአካባቢው አርሶ አደሮችን በማደራጀትና ግንዛቤ በመፍጠር የፍራፍሬ ልማት ስራ አዋጭ መሆኑን ከግንዛቤ አስገብተው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።