ቀጥታ፡

የሉሲ ሙዚየም ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በቅንጅት ይሰራል      

ሰመራ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የሉሲ ሙዚየም ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ  በቅንጅት  እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር  ህይወት ሐይሉ ገለጹ።

በአፋር ክልል የሚገነባው የሉሲ ሙዚየም ለአርኪኦሎጂስቶችና የታሪክ ተመራማሪዎች የዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የምርምር ማዕከል በመሆን ከማገልገሉ ባለፈ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን በመሳብ የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ቅርሰ ባለ ስልጣንና የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ በትናንትናው ዕለት የሉሲ ሙዚየም ግንባታ ፕሮጀክት የውል ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።


 

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ህይወት ሐይሉ ለኢዜአ እነደገለጹት የሉሲ ሙዚየም ግንባታን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በቅንጅት ይሰራል።

ባለስልጣኑ ለፕሮጀክቱ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፣ በቀጣይነት ትላልቅ የምርምር ስራዎች የሚከናወኑበት ማዕከል እንደሚሆንም አስረድተዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም የሱልጣን ዓሊሚራህ ሐንፈሬ ቤተ-መንግስት ዕድሳትን ጨምሮ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰው፣ አሁንም ከሙዚየሙ ግንባታ ጋር ተያይዞ ተጓዳኝ ስራዎችን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።


 

በባለሰልጣኑ የቅርስ አስተዳደር መሪ ስራ አሰፈፃሚ  ፀሃይ እሼቴ እንዳሉት፤ የሙዚየሙ መገንባት ለሃገርም ሆነ ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ሙዝየሙ ቅርሶችና ሌሎች መረጃዎች በተገቢው ጥንቃቄ እንዲቀመጡና እንዲጠበቁ ከማድረግ ባለፈ የክልሉን ቅርሶች ለማደራጅት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የሙዚየሙ ስራ መጀመር የሰው ዘር አመጣጥና የአፋርን ባህል ለማጥናት ለሚፈልጉ አካላት የመረጃ  ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ አቶ ኢብራሂም ሁመድ ናቸው።


 

የሙዚየሙ መገንባት  የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማሳደግ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም