ቀጥታ፡

በቡና ክላስተር የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል

አረካ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናን በክላስተር በማልማት የአርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው ተግባር መጠናከር እንዳለበት የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ።

ቡናን በክላስተር ማልማት ላይ ያተኮረ ክልላዊ የቡና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ በወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ አቹራ ቀበሌ ተካሂዷል።


 

"የቡና ምርት ዕድገት ለኢኮኖሚያችን" በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደ የችግኝ ተከላ መርሀግብር ላይ ‎የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንደገለጹት፤ በመንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው ብዝሃ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ግብርና አንዱ ነው። 

ከግብርና ምርቶች መካከል ቡና የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቅሰው፣ ቡናን በክላስተር ለማልማት የተጀመረው ሥራ ልማቱን ከማዘመን ባለፈ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በእጥፍ ስለሚያሳድገው መጠናከር አለበት ብለዋል።

‎የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በማስፋፋትና የግብርና ስራውን በማዘመን ለምርታማነት መጨመር ሁሉም በተለይ የዘርፉ አመራር መረባረብ አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል።


 

ህብረተሰቡ ውሃ ገብ ከሆኑ አካባቢዎች ባህር ዛፍና ያረጁ ቡናዎችን በመንቀልና በመጎንደል የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚ እንዲሆን የባለሙያዎች ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።

‎በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ‎የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቡና ላይ መስራት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።  


 

ለዚህም ‎ዘንድሮ በክልል አቀፍ ደረጃ ከ40 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቅሰው፣ በቡና ከሚለማው መሬትም 5 ሺህ ሄክታሩ በኩታ ገጠም እንደሚለማ አመልክተዋል።

በክልሉ በባህር ዛፍ የተሸፈኑ ማሳዎችን በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች የመቀየር ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ያሉት ኃላፊው ዘንድሮ ከሚተከሉ የቡና ችግኞች መካከል 34 ሚሊዮን የሚሆነው በተያዘው ሚያዚያ ወር የሚተከል ነው ብለዋል።

‎‎የቡና ልማቱ የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ለብዙዎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሠማ (ረ/ፕሮፌሰር) ናቸው።

‎ይህንን ለማጠናከር ለዘንድሮ የበልግ ወቅት ከ6 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ዝግጅት፣ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ፣ የኮምፖስት እና የጥላ ዛፎች ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።


 

‎ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ በልዩ ንቅናቄ 2ሺህ 253 ሄክታር የነባር ቡና ማሳ ዕድሳት ሥራ እና ከ2 ሺህ በላይ ሄክታር አዲስ የቡና ማሳ ዝግጅት ተከናውኗል ብለዋል።

‎‎በዞኑ በተለያዩ ክላስተሮች 1 ሺህ 207 ሄክታር ማሳ ላይ በኩታ ገጠም ቡና ተክሎ ለማልማት ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ትግበራ መገባቱንም ጠቁመዋል።

በዛሬው የተከላ መርሃ ግብር ከተሳተፉት ነዋሪዎች መካከል አቶ ዘለቀ ስኔቦ እና መጋቤ ተስፋዬ ሹኬ፤ ከዚህ ቀደም ቡናን በባህላዊ መንገድ ስለሚያመርቱ ከልማቱ ብዙም ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል።

ከዘርፉ ባለሙያዎች በተሰጣቸው ትምህርት መሰረት የባህር ዛፍ ቦታን በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች በመተካታቸው የተሻለ ምርት ማግኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በተለይ ቡናን በክላስተር ማልማት ድካምንና ያለአግባብ ይባክን የነበረን ጊዜ በመቀነስ ተጠቃሚነትን ስለሚያሳድግ አጠናክረው ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

በቡና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችና የወረዳው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም