በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዝግጅት ላይ ከሚገኙ ችግኞች መካከል 70 በመቶው የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዝግጅት ላይ ከሚገኙ ችግኞች መካከል 70 በመቶው የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው
በጋምቤላ ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት እየተዘጋጁ ከሚገኙት ችግኞች መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በ70 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ እንደሆነ ቢሮው ገልጿል።
በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ኬት ቾል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያግዙና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላላቸው ችግኞች ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም 70 በሚሆኑ የግልና የመንግስት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እየተዘጋጁ ከሚገኙት ችግኞች መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከችግኞቹ መካከል ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ ፣ ዘይቱናና ሎሚ ዋነኞቹ እንደሆኑም ገልጸዋል።
ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት እየተዘጋጁ ካሉት የፍራፍሬ ችግኞች ባለፈ ከአካባቢው የአየር ንብረት ጋር የሚጣጣሙ የደን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በበጋው ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የተከናወነባቸው ከዘጠኝ ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆቱ አካባቢዎችን ስነ-ህይወት ለማልበስ የመረጣና የቦታ ልየታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተተከሉት የፍራፍሬና ሌሎች ችግኞች የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ከመቀየር ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በቀጣይም በክረምቱ ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በሚያግዙ ችግኞች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።