ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 11 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ገብተዋል

ጎንደር ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦በጎንደር ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 11 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።   

በከተማው በ400 ሚሊዮን ብር ወጪ በአንድ ባለሀብት የተገነባ የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።     

የመምሪያው ሃላፊ ግርማይ ልጃለም እንዳሉት፤ በዘንድሮው ዓመት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 20 መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርት ማምረት ለማሸጋገር እየተሰራ ነው።  

 

ባለፋት ዘጠኝ ወራት በተደረገ የተቀናጀ ጥረትም 10 መካከለኛና አንድ ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪ ወደ ማምረት እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።  

ወደ ምርት እንዲገቡ የተደረጉት ኢንዱስትሪዎችም በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማምረት ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ያስቻሉ ሲሆን ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ እንደሆኑም ገልጸዋል።    


 

አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውም ገበያን በማረጋጋት፣ ተኪ ምርቶችን በማምረትና የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም አመልክተዋል።    

በከተማው የሰፈነው ሠላም አምራች ኢንዱስትሪዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ያሉት ደግሞ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው።   


 

የከተማ አስተዳደሩ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የግንባታ መሬት ከማዘጋጀት ጀምሮ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።   

የዘይት ፋብሪካው ባለቤት አቶ አደራጀው ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ፋብሪካው በቀን 20 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው ተናግረዋል።   
 

ፋብሪካው በቀን 400 ኩንታል አኩሪ አተር በጥሬ እቃነት የሚጠቀም ሲሆን ይህም በግብርና ስራ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች አስተማማኝ የገበያ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።   

በአሁኑ ወቅት ለ30 ወገኖች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ 400 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸው 7 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መገንባቱንም ጠቁመዋል።   

በስነ ስርዓቱ ላይም የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም