ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የማይበገር የምግብ ስርዓት እየገነባች ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች በሚገባ በማወቅና በማልማት ለዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የማይበገር የምግብ ስርዓት እየገነባች መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

ላለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የባለብዙ ዘርፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ፣ ዘርፉ አስደናቂ የምርት እድገትና መዋቅራዊ ሽግግር እያስመዘገበ ይገኛል።

በተለይም በበጋ ስንዴ እና በመስኖ ልማት ረገድ በስፋት የተከናወኑት ተግባራት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የስንዴ አምራች ሀገር እንድትሆን ያስቻሉ ሲሆን፣ ይህም በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ አፋጥኖታል።

ይህ ስኬት ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የኢኮኖሚ ጥንካሬዋን እና የግብርና ምርታማነት አቅሟን በተግባር ያሳየ ሆኗል።

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሀገርን የምግብ ሉዓላዊነት በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የምርትና ምርታማነት እድገት መሰረታዊ ነው።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ስንዴ ከውጭ ገዝታ ለማስገባት ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ማስቀረት መቻሏን ገልጸዋል።

መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ምርትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት፣ በግዥ ከውጭ ይገባ የነበረውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እንደተቻለ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ይህ ታሪካዊ ስኬት የሀገሪቷን የውጭ ምንዛሬ ከመታደጉ ባለፈ ራስን በምግብ ለመቻል ለተያዘው ብሄራዊ ግብ ትልቅ እርምጃ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በምርምር፣ በግብርና ግብዓቶች አቅርቦት እና በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ረገድ ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በተለይም የማዳበሪያ አቅርቦትን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው የፋብሪካ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የምርታማነት ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆነና በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸው ምርጥ ዘሮች በራስ የምርምር አቅም ማውጣት የሚያስችል የግብርና ምርምር ስርዓት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የመሬት፣የውሃ እና የሰው ሃይል አቅም በማቀናጀት ለግብርናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ የሃይል እና የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ለማሟላት የምታደርገው ጥረት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ነው ያስገነዘቡት።

አንድ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የጂኦፖለቲካ ለውጦች በነዳጅ አቅርቦትና በምግብ ሉዓላዊነት ላይ የሚያስከትሉትን ብርቱ ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል ስራ በትኩረት መከናወን እንዳለበት አንስተዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋዎች በሚገባ ለይታ በማወቅና በማልማት፣ ማንኛውንም ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ቀውስ መቋቋም የምትችል ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህም ከውጭ የሚመጡ ተጽዕኖዎችን ተቋቁማ የምግብ ሉዓላዊነቷን በተገቢው መንገድ እንድታረጋግጥ የሚያስችላት መሆኑንም ገልጸዋል።

የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ጠንካራ ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት አርሶና አርብቶ አደሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም