በአፋር ክልል የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት እንዳይስተጓጎል በግብረ-ኃይል የታገዘ ቁጥጥር እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት እንዳይስተጓጎል በግብረ-ኃይል የታገዘ ቁጥጥር እየተደረገ ነው
ሰመራ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጠር በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ መዲና ማህሙድ እንደገለጹት፤ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ የሚመራውና የተለያዩ ተቋማትን ያቀፈው ግብረ-ኃይል፣ ህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎትን ያለ እንግልት እንዲያገኝ እየሰራ ይገኛል።
በተለይም ስትራቴጂካዊ በሆነው የኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ላይ ለሚንቀሳቀሱ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ቅድሚያ በመስጠት አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኃላፊዋ አክለውም ዘርፉ ከተለያዩ መስኮች ጋር ትስስር ያለው በመሆኑ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከማህበራትና ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በቢሮው የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሁሴን ቦልኮ በበኩላቸው፤ ግብረ-ኃይሉ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ከመቆጣጠር ባለፈ፣ ከተፈቀደው በላይ ተጨማሪ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ታንከር ይዘው በሚገኙ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ሳጅን መሐመድ አህመድ፤ በማደያዎች አካባቢ የሚታየውን የወረፋ መጨናነቅ ለመቀነስና ሊከሰቱ የሚችሉ የትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል ፖሊስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።