መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሰራተኞችን የስራ ባህል አሻሽሏል - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሰራተኞችን የስራ ባህል አሻሽሏል
አዳማ ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦በአዳማ ከተማ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የሰራተኞችን የስራ ባህል ማሻሻሉን የአገልግሎቱ ስራ አስኪያጅ ገለጹ።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ መኩሪያ ድንቁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማው 138 አገልግሎቶች በመሶብ አንድ ማዕከል ውስጥ እየተሰጡ ነው።
በዚህም 31 የሚሆኑ የአስተዳደሩ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ የተቀናጀ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።
በማዕከሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀናጀ ፈጣን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እየተቻለ መሆኑን ጠቁመው፤ ለተገልጋዮችም ምቹና ፅዱ በሆነ አካባቢ አገልግሎት ማግኘት ማስቻሉን ተናግረዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩ የሰራተኞችን የስራ ባህል ከመለወጡም ባለፈ የመንግስት የስራ ሰዓትን በአግባቡ የመጠቀም ዝንባሌ እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል።
በማዕከሉ 18 የሚሆኑ የለሙ ቴክኖሎጂዎች በተሟላ መልኩ የኦንላይን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፤ የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሠራተኞችን አቅም በቴክኖሎጂ የማብቃት ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በከተማዋ ደረጃ ካለው ማዕከል ባለፈ በዳቤ፣ በአባ ገዳና በቦሌ ክፍለ ከተሞች የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን ማስፋፋት ተችሏል ብለዋል።
በአዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሲገለገሉ ያገኘናቸው አቶ አብረሃም ወይሴ፤ ለመሬት ጉዳይ አገልግሎት ለማግኘት ፈልገው መምጣታቸውን ገልጸዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ችግሮች እንደነበሩ አንስተው፤ በተለይ ከአንድ መስሪያ ቤት ወደ ሌላው የሚደረገው ጉዞ እና ምልልስ ፈታኝ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ሁሉንም አገልግሎት በአንድ መስኮት እያገኘን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ወይዘሮ አለምነሽ ሽብሩ በበኩላቸው "ከበር ጀምሮ ያለው አቀባበልና ማስተናገጃው በጣም ደስ የሚል ነው" በማለት ይገልጻሉ።
በምቹ ማዕከል የተቀላጠፈ አገልግሎት በማግኘታቸው መደሰታቸውንም ተገልጋዮቹ ገልጸዋል።