ለሀገርና ለሕዝብ የሚሰራን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገርና ለሕዝብ የሚሰራን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - አርሶ አደሮች
ደሴ ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ለሀገርና ለሕዝብ የሚሰራን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን የተሁለደሬ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው ዓመት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው።
ከዚህ ውስጥም የእጩዎች ምዝገባ የተጠናቀቀ ሲሆን የመራጭነት ምዝገባ ሂደት ደግሞ እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ/ም እንደሚካሔድም መገለጹ ይታወሳል፡፡
የወረዳው አርሶ አደሮች እንደሚሉት የምርጫ ካርድ በማውጣት በመጪው ምርጫ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት አድርገዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት ውስጥ አርሶ አደር ሰይድ ፈንታ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ እና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ይወክለኛል ያልኩትን ፓርቲ ወደ ስልጣን በማምጣት ሀገሪቷን እንዲመራ በካርዴ ለመወሰን እየተጠባበኩ እገኛለሁ ብለዋል።
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅም ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
አርሶ አደር መሀመድ አደም በበኩላቸው፣ በምርጫው የሚጠበቀውን ተሳትፎ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ነው የሚናገሩት።
በምርጫው ቀን ይጠቅመናል፣ ይበጀናል ለምንለው ፓርቲ ድምጻችንን ለመስጠትና የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት እየተጠባበቅን እንገኛለን ሲሉም ተናግረዋል።
ህገ-መንግስቱ ያጎናጸፈንን መብት ከመጠቀም ባለፈ ዴሞክራሲያዊ ልምምዱ በተሻለ መንገድ እንዲከወንና ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን ነው ያሉት።
የመራጭነት ካርድ መውሰድ ለምንፈልገው ፓርቲ ድምጻችንን ለመስጠት ቁልፍ ተግባር ነው ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ሉባባ መሀመድ ሲሆኑ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎችም በቀሪ ጊዜያት ተመዝግበው ቢዘጋጁ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።