ቀጥታ፡

የአርባ ምንጭ ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋ ያላትን ውበት ይበልጥ በማጉላት ለጉብኝት የበለጠ ተመራጭ ያደርጋታል 

አርባ ምንጭ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦የአርባ ምንጭ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋ ያላትን ውበት ይበልጥ በማጉላት ለጉብኝት የበለጠ ተመራጭ እንደሚያደርጋት ተመለከተ፡፡ 

በከተማዋ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው።

አርባ ምንጭ ከተማን ለኑሮ፣ ለሥራ፣ ለጉብኝትና መዝናናት የሚመርጧት አስተማማኝ የኢኮኖሚ ኮሪደር፣ ምቹና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተለያዩ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

የከተማዋ ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በከተማዋ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና ከነዚህ ውስጥም ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍነው የኮሪደር ልማት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ልማቱ ከተማዋ ያላትን ውበት ይበልጥ ከማጉላት ባለፈ ክፍለ ከተሞችን እርስ በርስ የሚያገናኝና ከተለያዩ የቱሪዝም መስህብ ሥፍራዎች ጋር የሚያስተሳስር እንደሆነም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የመንገድ ዳር ማረፊያዎች፣ ፐብሊክ ፕላዛዎች፣ የእግረኛ መንገድ፣ የአይነ ስውራንና የአካል ጉዳተኛ መተላለፊያ፣ የብስክሌት መንቀሳቀሻ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የመዝናኛ ስፍራና የንግድ ቦታዎችን ባካተተ መልኩ እየተገነባ መሆኑንም ከንቲባው አስረድተዋል።

እንደ ከንቲባ መስፍን (ዶ/ር) ገለጻ የኮሪደር ልማቱ የአካባቢውን ሕዝብ ባህል፣ እሴትና የተፈጥሮ ፀጋ ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከናወነ ነው።

የኮሪደር ልማቱ ስራ በአሁኑ ወቅት 50 በመቶ ላይ እንደደረሰና ዋና ዋና ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ገልጸው፣ አጠቃላይ ስራውን እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ 24 ሰዓት ያለማቋረጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  


 

ግንባታው ሲጠናቀቅ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለኑሮ፣ ለቱሪዝምና ለሥራ ይበልጥ ምቹ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።

የከተማው ነዋሪዎች ወደመንገድ የወጡ አጥሮችና ቤቶችን በማንሳት እንዲሁም በልማቱ እየተሳተፉ ያሉ ሠራተኞችን በማበረታታት እያደረጉት ላለው ትብብርም ከንቲባው አመስግነዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት ባዩ፤ የኮሪደር ልማት ሥራው የከተማዋን ውበት ይበልጥ ከማድመቅ ባለፈ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።


 

ከዚህ ቀደም ከመንገድ ጥበት የተነሳ ከተሽከርካሪ ጋር እየተጋፋን ስንጓዝ ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፣ በአሁኑ ወቅት የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገድ በመለየቱ በነጻነት ለመንቀሳቀስ እንደቻሉና የተሽከርካሪ አደጋም እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

በየአካባቢው የማረፊያና የመዝናኛ ስፍራዎች መዘጋጀታቸው የደከመ ሰውነትን ለማሳረፍ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ መንገዱ ለእግር ጉዞ ምቹ መሆኑ ጤናን ለመጠበቅ እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ደረጃ ከፍ ከማድረግ በላይ አኗኗራችንን ለማዘመን አግዞናል ያሉት ደግሞ አቶ ታጠቅ ሌሎ ናቸው። 


 

በከተማዋ እየታየ ባለው የልማት ውጤት መደሰታቸውን ገልጸው፣ የኮሪደር ልማት ሥራ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑ የህዝቡ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲጠናከር ማድረጉን ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ የኮሪደር ልማቱ ስኬታማ እንዲሆን ከአስተዳደሩ ጎን በመቆም እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም