በዞኑ ለጠቅላላ ምርጫው የወጣቶችን ተሳትፎ ማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ለጠቅላላ ምርጫው የወጣቶችን ተሳትፎ ማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
መቱ ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወኑ መሆናቸውን በኢሉአባቦር ዞን የሚገኙ የወጣት አደረጃጀቶች ገለጹ።
የኢሉአባቦር ዞን ወጣቶች ፌዴሬሽን ሊቀመንበር አበበ ሆርዶፋ ለኢዜአ እንዳለው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶች ተሳትፎ የጎላ ሚና አለው።
ለዚህም ለዞኑ ወጣቶች በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድሕረ-ምርጫ ሂደቶች በንቃት እንዲሳተፉ የምርጫ ሥነ-ምግባር ትምህርቶች ላይ በማተኮር ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው ብሏል።
ምርጫ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ወጣቱ ለስኬታማነቱ የድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግም ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብሏል።
የዞኑ ወጣቶች ማሕበር ሊቀመንበር ቢቂላ ኮይና በበኩሉ፤የዞኑ ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።
በተለይ የወጣቶችን አደረጃጀቶች በማጠናከር የመምረጥ፣ የመመረጥና የምርጫ ታዛቢነት መብታቸውንና የዜግነት ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ነው ያመለከተው።
በዋናነትም ወጣቱ በምርጫው ሒደት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ተሳትፎ እንዲኖረው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።
የወጣቱን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጸው።