ቀጥታ፡

የአፕል ልማት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ፈጥሮልናል-የጌዴኦ ዞን አርሶ አደሮች

ዲላ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የአፕል ልማት ለአካባቢያቸው ስነ-ምህዳር ተስማሚ ከመሆን ባለፈ ተጨማሪ ገቢ እያገኙበት መሆኑን በጌዴኦ ዞን የቡሌና የጮርሶ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ የአፕል ልማትን በማስፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በ72 ሄክታር መሬት ላይ ከ45 ሺህ በላይ ችግኞች ተከላ እየተከናወነ መሆኑም ተመላክቷል።


 

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአካባቢው ባለው የመሬት ተዳፋትነት ምክንያት የአፈር መሸርሸር እንዳያጋጥምና ለምነቱን በመጨመር ረገድ የአፕል ዛፍ የራሱን ሚና እየተጫወተ ነው።

በዚህም ዛፉ የአካባቢያቸውን ስነ-ምህዳር በመጠበቅ ከቋሚና ዓመታዊ ሰብሎች በተጨማሪ ገቢ እያስገኘላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ አርሶ አደሮች መካከል በዞኑ የቡሌ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሽፈራው መንገሻ ፤ከመንግስት ባገኙት የሙያና የችግኝ ድጋፍ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ወደ አፕል ልማት መግባታቸውን ገልጸዋል።


 

በአሁኑ ወቅት በአምስት ዓይነት የተለያዩ ዝርያዎች ከ50 በላይ የአፕል ዛፎች ምርት እየሰጡ እንደሚገኙ አንስተው ምርቱ ከቤተሰብ ፍጆታ አልፎ በዓመት ከአንዱ የአፕል እግር ከ2 ኩንታል በላይ ምርት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዚህም ከ200 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ እንደሚገኙ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋት እየጣሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰብል ማሳቸው ዙሪያ ያለሟቸው የአፕል ችግኞች ለምርት ደርሰው ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደፈጠሩ ያነሱት ደግሞ  የቡሌ ወረዳ አርሶ አደር አብርሃም ሃይሉ ናቸው።


 

እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ የአፕል ዛፍ ተዳፋት የሆነውን መሬት በጎርፍ እንዳይጠረግ በማድረግ ለምነቱ እንዲሻሻል እያገዘ ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ የአፕል ችግኞችን ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የችግኝ ጣቢያ በመውሰድ ተከላ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።


 

‎‎የጮርሶ ወረዳ አርሶ አደር አየለ ጅግሶ በበኩላቸው፤ በጓሯቸው ከተከሉት አፕል በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን እያስተማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

‎የአፕል ልማት ከሚያስገኘው ተጨማሪ ገቢ ባለፈ ለአካባቢው ሥነ ምህዳር ተስማሚ በመሆኑ ልማቱን ለማስፋት ችግኝ እየተከሉ መሆኑን ገልጸዋል።

‎በዞኑ አራት ደጋማ ወረዳዎች በ334 ሄክታር መሬት ላይ አፕል እየለማ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በድሉ አየለ ናቸው።


 

ከዚህም በዓመት ከ30 ሺህ 200 ኩንታል በላይ ምርት ለገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

ልማቱን በማስፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግም በተያዘው ዓመት በ72 ሄክታር መሬት ላይ ከ45 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የአፕል ዝርያዎችን በመጠቀም የልማት ስራው እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።

በተለይም በዘርፉ ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ ልማቱ በማስገባት ሃብት እንዲያመነጩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም