ቀጥታ፡

በክልሉ በአካልና በአዕምሮ ብቁ የሆነ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሐረር፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በአካልና በአዕምሮ ብቁ የሆነ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

"በአካል የበቃ በአዕምሮ የነቃ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና" በሚል መሪ ሐሳብ የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ 2ኛው ክልል አቀፍ የትምህርት ቤቶች ሊግና የመምህራን ስፖርት  ውድድር ተጀመረ።


 

በውድድሩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንዳሉት የዛሬ ተማሪዎች የነገዋን ኢትዮጵያ ተረካቢ ትውልድ ናቸው።

በአካልና በአዕምሮ ብሩ የሆነ ትውልድ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ያለው ሚና ከፍተኛ ስለሆነ ጠንክሮ መስራት፣ ማንበብ፣ መመራመርና  ለቤተሰብና ለሀገር አለኝታ መሆን ይገባል ብለዋል።

ስፖርት ለጤንነት ብቻ ሳይሆን ለአእምሯዊ ብስለትና እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን ጠቁመው፤  ተማሪዎችም ይህን ተገንዝበው ለተግባራዊነቱ ሊተጉ ይገባል ብለዋል።


 

ተማሪዎች ማህበራዊ ሚዲያ የሚመራቸው ሳይሆኑ በስነ ምግባር የታነጹና ማህበራዊ ሚዲያውን የሚመሩ መሆን እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ስፖርት ለወዳጅነት፣ ለአንድነትና ለሰላም ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በውድድሩ ጠንካራ ፉክክር በማድረግ በስፖርታዊ ጨዋነት ማከናወን ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ በበኩላቸው ፤ ከዛሬ ሚያዝያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ሳምንታት በሚቆየው በዚሁ ውድድር በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።


 

ውድድሩም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ጤናማና ንቁ ትውልድ ለመፍጠር ያለንን ቁርጠኝነት የምናሳይበት ነው ብለዋል።

እንዲሁም በተማሪዎችና መምህራን  መካከል ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር እና ክልል አቀፍ ስፖርተኞችን ለማፍራት ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱን አቶ ጌቱ ገልጸዋል።

በውድድሩ  ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ በክልሉ የሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መምህራንና የስፖርት ባለሙያዎች ተገኝተዋል። 

ውድድሩ ዛሬ በከተማው በሚገኘው ኢማም አህመድ ስታዲየም ሲጀመር በ100 ሜትር የመምህራን  ሩጫ  ውድድር አባድር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲያሸንፍ፤ በወረዳ ሴቶች ሸንኮር ወረዳ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አሁንም  አባድር ሁለተኛ ደረጃ  አሸናፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም