ቀጥታ፡

ዜጎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በቀሪ ቀናት እንዲወስዱ የበኩላችንን ሚና እየተወጣን ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9 /2018 (ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በቀሪ ቀናት በመውሰድ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መጋቢት 28/2018 ዓ.ም ሲያካሂድ ቆይቷል።

በተጨማሪም ቦርዱ የመራጮችን ምዝገባ ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም አራዝሟል።

በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ደግሞ ድምጽ የሚሰጥበት ዕለት ነው፡፡

በመሆኑም መራጮች በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ድምፅ መስጠት የሚያስቻላቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ምርጫ ዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን የሚያረጋግጡበት ሒደት ነው።


 

ይህም የዲሞክራሲ ባህልን በማዳበር ህዝብ የስልጣን ባለቤትነት መሆኑን በተግባር የሚረጋገጥበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ዜጎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ አስቻይ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ምክር ቤቱም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በምርጫው ዙሪያ ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።

ለአብነትም በምርጫው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያላቸውን የታዛቢነት ሚና እንዲወጡ በማድረግ ነጻ፣ተአማኒና ስኬታማ ምርጫ ለማከናወን የጋራ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም በጠቅላላ ምርጫው ሒደት የዜጎች ተሳትፎ የተረጋገጠበት እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ብለዋል።

እሸት ሀገር በቀል የህጻናትና ወጣቶች ልማት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ እንደገለጹት፥ ምርጫ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያጎለብቱበት ዕድል ነው።


 

በዚህም ድርጅቱ ዜጎች በቀሪ ቀናት የመራጭነት ካርድ በመውሰድ በምርጫው ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የግንዛቤ ፈጠራ እና መሰል ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም የምርጫ ካርድ መውሰድ መብት መሆኑን ማስገንዘብና በምርጫው ቀን ወጥተው እንዲመርጡ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እየተሰጡ መሆኑን አብራርተዋል።


 

ሴቭ ዩር ሆሊ ላንድ የተሰኘ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ዳይሬክተር የማነህ ጉሽ በበኩላቸው፤ ዜጎች የመራጭነት ካርድን በመውሰድ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ምርጫው ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን ወጣቶች ያላቸውን የማይተካ ሚና እንዲወጡ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በቀሪ ቀናትም ዜጎች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ እንዲወሰዱ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም