የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ) ፦ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው በኮዬ ፈጨ ኮንዶሚኒየም በተለያዩ ሳይቶች የሚገኙ ነዋሪዎችን በተናጠል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በኮዬ ፈጨ ኮንዶሚንየም ፕሮጀክት 11 እና 17 የሚኖሩ ከ12 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በየብሎኩ በተገጠመ ባለ ሦስት ፌዝ ቆጣሪ በጋራ ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሶ፤ በዚህም በኃይል ማነስና መቆራረጥ ሲቸገሩ ቆይተዋል ብሏል፡፡
አሁን ግን በተናጠል ቆጣሪ እንዲገጠምላቸው በመደረጉ በቂ ኃይል እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ብሏል በመረጃው፡፡
ነዋሪዎቹን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግም 17 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር፣ የ8 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ የመሬት ውስጥ ተቀባሪ መስመርና የ4 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ የአየር ላይ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን ገልጿል።
በዚህም 53 ትራንስፎርመሮች መተከላቸውንና ለነዋሪዎቹ 12 ሺህ 100 ቆጣሪዎች መገጠማቸውንም አረጋግጧል።
በቀጣይ በአዲስ አበባ ቤቶች በኩል የሚፈፀሙ ክፍያዎች እንደተጠናቀቁ በኮዬ ፈጨ ኮንዶሚኒየም በተለያዩ ሳይቶች የሚገኙ ነዋሪዎችን በተናጠል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክቷል።
አገልግሎቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ለማሳደግ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል።