በኦሮሚያ ክልል በበልግ አዝመራ እስካሁን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በበልግ አዝመራ እስካሁን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በበልግ እርሻ እስካሁን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ምርጥ ዘሮች መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አርሶ አደሩ በበልግ አዝመራው ውጤታማ እንዲሆን ሙያዊ ድጋፍ እና የግብዓት አቅርቦት በአግባቡ ቀርቧል።
በአሁኑ ወቅትም የበልግ አብቃይ አካባቢዎች የአንደኛና ሁለተኛ ዙር የማሳ ዝግጅት ተጠናቆ በዘር መሸፈን ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የበልግ አዝመራው እየተካሄደባቸው ከሚገኙ ዞኖች መካከል ምስራቅ ቦረና፣ ጉጂ፣ አርሲ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፣ ምስራቅ ባሌ እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች ይገኙበታል ብለዋል።
በተለይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡና ለመኽር አዝመራ መሬት የሚለቁ እንደ በቆሎ፣ ጤፍ፣ የቢራ ገብስ፣ ቦሎቄ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ ማሾና ሌሎች የሰብል አይነቶች መልማታቸውን አንስተዋል።
በክልሉ በበልግ እርሻ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት ከ46 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱንም አስታውሰዋል።
በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የአገዳ፣ የብርዕና የጥራጥሬ ሰብሎች መሸፈኑን ተናግረዋል።
በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል በኩታ ገጠም መልማቱን ጠቅሰው አጠቃላይ የበልግ እርሻው ስራ 87 በመቶ መድረሱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የቀሩት አካባቢዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዘንድሮ በልግ እርሻ የዝናብ ሁኔት አመቺ በመሆኑ ከልማቱ በቂ ምርት የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
ለበልጉ ልማት ከተሰራጨው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን 366 ሺህ ኩንታል ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።