ሪፎርሙ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተናዎችን የመቋቋም አቅሙ እንዲጠናከር አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ሪፎርሙ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተናዎችን የመቋቋም አቅሙ እንዲጠናከር አድርጓል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገር በቀል ሪፎርሙ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ፈተናዎችን የመቋቋም አቅሙን ማጠናከሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ (ዶ/ር) ገለጹ።
የ2026 የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የፀደይ ወቅት ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አይኤምኤፍ “ከአዲሱ ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ስነ-ምህዳር ጋር መጣጣም” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ከፍተኛ የፓናል ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
በወቅቱም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አቅርቦት በተገደበበት በዚህ ወቅት፣ በሀገር በቀል የሪፎርም እርምጃዎች አማካኝነት ፈታኝ ሁኔታዎችን እንዴት እየተወጣች እንደምትገኝ አብራርተዋል።
እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በንግግራቸው የኢትዮጵያን አጠቃላይ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ዋና ዋና ነጥቦች አንስተዋል።
ሪፎርሙ የምንዛሬ ተመን ማዕቀፍን ማጠናከር፣ የገንዘብ ፖሊሲን ማዘመን፣ የሀገር ውስጥ ሀብት አሰባሰብን ማሳደግ እና ኢኮኖሚው ይበልጥ በግል ዘርፍ የሚመራ እንዲሆን ለማድረግ የሚከናወኑ መዋቅራዊ ሪፎርሞችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢኮኖሚው የመቋቋም አቅም መጠናከር በወጪ ንግድ፣ በውጭ ምንዛሬ ክምችትና በገቢ አሰባሰብ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የባንኩ ገዥ አመልክተዋል።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሪፎርም በሀገር ውስጥ ባለቤትነት የሚመራ ቢሆንም፣ የልማት አጋሮች የሚያደርጉት የተቀናጀ ድጋፍ ለውጤታማነቱ አስፈላጊ መሆኑን ገዢው አስገንዝበዋል።
በተለይም ዓለም አቀፋዊ አለመረጋጋት በግልጽ በሚታይበት በዚህ ወቅት፣ ሀገራዊ የልማት ጥረቶችን ለማሳካት የልማት አጋሮች የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ይህ የፓናል ውይይት ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመጠበቅ፣ ሪፎርሞችን ለማስቀጠል እና ተለዋዋጭ በሆኑ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች ውስጥ ይበልጥ ጠንካራና ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም ያረጋገጠ ሆኗል።
ገዢው በሀገር ደረጃ እያደገ የመጣውን የለውጥና የብልጽግና ፍላጎት በማንሳት፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት (Beacon) የመሆን ጉዞ ላይ እንደሆነች ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አይበገሬነት አድናቆት እንዳገኘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል።