በኦሮሚያ ክልል አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘ ነው
ቢሾፍቱ ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ አጠቃላይ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በበርካታ ዘርፎች ውጤታማ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በክልሉ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቀነስ ተጨባጭ ውጤት እየተገኘበት ነው ብለዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም በ5 ከተሞች በሙከራ ደረጃ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማ በመሆኑ፣ ተሞክሮውን የማስፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን ወደ 26 ከተሞች ማስፋት ተችሎ አንዳንዶቹ አገልግሎት መጀመራቸውን ገልጸው፤ በሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ በ60 ከተሞች ለማስጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያገኙ ዜጎች ከ97 በመቶ በላይ እርካታ እንዳላቸው የገለጹት አቶ አወሉ፤ ይህ አርአያነት ያለው ሥራ ተስፋፍቶ ሕዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
ለሥራው ስኬታማነትም ቴክኖሎጂን፣ የሰው ኃይልን፣ የሥራ ቦታንና አሠራርን በማመቻቸት ረገድ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
አመራሩ ወደ ሕዝቡ ቀርቦ እንዲያገለግልም፣ የጉዳይ ፈጻሚ ቀናትን ከመለየት ባለፈ በወረዳዎችና በቀበሌዎች በተደረገው ሪፎርም ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ መመቻቸቱን ጠቁመዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ እና ውጤታማ ማድረግ እንዲቻልም የመልካም አስተዳደር ችግር በሚፈጥሩ ሰራተኞች ላይ የተለያዩ የእርምት እርምጃዎች መወሰዳቸውን አንስተዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ237 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸው፤ በቀጣይም የክልሉን ገቢ ለማሳደግ ለግብር ከፋዮች ግንዛቤ የመፍጠርና የገቢ ምንጮችን የመፈተሽ ስራ ይጠናከራል ብለዋል።
በተመሳሳይ በክልሉ በበጀት ዓመቱ ከ28 ሺህ 800 በላይ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረው፤ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል 21 ሺህ የሚሆኑት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።