ኢትዮጵያ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ከቱርኪዬ ጋር ዛሬ ትጫወታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ከቱርኪዬ ጋር ዛሬ ትጫወታለች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ያዘጋጀው የ"UEFA Frendship Cup" ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር ዛሬ ይጠናቀቃል።
ውድድሩ በቱርኪዬ ከመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ ቆይቷል።
በወዳጅነት ዋንጫው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ለማጠናቀቅ ከቱርኪዬ ጋር ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ትጫወታለች።
በምድብ ሁለት ጨዋታዋን ያደረገችው ኢትዮጵያ በምድቧ ሶስት ጨዋታዎችን አድርጋ ሁለቱን ስታሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥተዋል። በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በምድብ አንድ የተደለደለችው ቱርኪዬ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
በአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የውድድር ደንብ መሰረት ከየምድቡ ሁለተኛ የወጡ ሀገራት ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት ይጫወታሉ።
ከጨዋታው በፊት ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ የሚመራው ቡድን በውድድሩ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል።
ብሔራዊ ቡድኑ መልካም ጉዞውን ለማሳመር ከቱርኪዬ ጋር ለደረጃ ይጫወታል።
ከየምድቡ አንደኛ የወጡት ፓራጓይ እና ኖርዌይ ዋንጫውን ለማንሳት ዛሬ ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ፣ ኮስታሪካ፣ ዩራጓይ፣ ኖርዌይ፣ ቱርኪዬ፣ ፓራጓይ፣ ሞሮኮ እና ኡዝቤኪስታን በውድድሩ ላይ የተሳተፉ ሀገራት ናቸው።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ያዘጋጀው የወዳጅነት ዋንጫ ከውድድር ባለፈ የክፍለ አህጉራዊ እግር ኳስ ልማት ትብብርን ማጠናከርን ያለመ ነው።
በተጨማሪም የእርስ በእርስ የልምምድ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን የተለያዩ ስልጠናዎች እና ጉብኝቶችም የውድድሩ አካል ነበሩ።